“ዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ ደህንነት ማዕከል” ማቋቋም እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ተናገሩ

2 Mons Ago
“ዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ ደህንነት ማዕከል” ማቋቋም እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ተናገሩ
አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የመረጃ መረብ ጥቃት በጋራ ለመከላከል “ዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ ደህንነት ማዕከል” ማቋቋም እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) ተናገሩ።
 
“ፖዘቲቭ ቴክኖሎጂ” የተሰኘው የሩስያ የመረጃ መረብ ደህንነት ኩባንያ ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ ደህንነት አውደ ርዕይ በሩስያ ሞስኮ እየተካሄደ ነው።
 
በመድረኩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ሚኒስትር ዴኤታው፤በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እየተገናኘ ባለ ዓለም ውስጥ የመረጃ መረብ ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
 
የአፍሪካ ሀገራትም የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን አንስተው፤ይህንን አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የመረጃ መረብ ጥቃት በጋራ ለመከላከል “ዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ ደህንነት ማዕከል” ማቋቋም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
 
ኢትዮጵያ በተከለሰው የሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፖሊሲ እንዲሁም በዲጂታል ስትራቴጂዋ ውስጥ የመረጃ መረብ ደህንነትን ቁልፍ ጉዳይ አድርጋ ማስቀመጧን ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።
 
አያይዘውም ኢትዮጵያ በአህጉር አቀፍ ደረጃ የአፍሪካ የመረጃ መረብ ደህንነት ላይ የሚያተኩረው የማላቡ ስምምነት ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለመፈረም ከጫፍ መድረሷንም ተናግረዋል።
 
እ.ኤአ በ2013 በዓለም አቀፍ ደረጃ 113 ቢሊዮን ዶላር የቀጥታ የመረጃ መረብ ወንጀል እንደተፈጸመ የተገለጸ ሲሆን ይህ አሃዝ በ2025 ወደ 10.5 ትሪሊዮን ሊደርስ ይችላል የሚሉ ግምቶች እንዳሉ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።
 
በሩስያ ሞስኮ እየተካሄደ የሚገኘው የመረጃ መረብ ደህንነት አውደ ርዕይ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች እና የፖሊሲ አውጭዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top