በክልሉ የትምህርት መሠረተ ልማትን ለማሟላት እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት እያመጣ ነው - ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

22 Days Ago
በክልሉ የትምህርት መሠረተ ልማትን ለማሟላት እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት እያመጣ ነው - ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የትምህርት መሠረተ ልማትን ለማሟላት እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በክልሉ ዋቻ ከተማ የተገነባው የ'ቦባ ቆጫ' አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተመረቀበት ወቅት ነው።

ትምህርት ቤቱ በገቢዎች ሚኒስቴርና በጉምሩክ ኮሚሽን በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነባ ሲሆን 11 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ተገልጿል።

ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ በትምህርት ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግስትና ኅብረተሰቡ በቅንጅት እየሰሩ ነው።

በዚህም የትምህርት መሠረተ ልማት ማሟላት ተግባር ውጤት እያመጣ መሆኑን በመጥቀስ ርብርቡ ይጠናከራል ብለዋል።

በክልሉ 'ቦባ ቆጫ' ቀበሌ ተገንብቶ ለተጠናቀቀው ትምህርት ቤት ድጋፍ ያደረጉ የገቢዎች ሚኒስቴርንና የጉምሩክ ኮሚሽንን በክልሉ መንግስት ስም አመስግነዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው በክልሉ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በ"ትምህርት ለትውልድ" ንቅናቄ በርካታ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አንስተዋል።

እስካሁን በተከናወነ ስራ ከ414 ሚሊዮን የሚበልጥ ገንዘብ ተሰብስቦ የተለያዩ የትምህርት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ ሚኒስቴሩ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የትምህርት ቤት ግንባታውን ማከናወኑን ተናግረዋል።

በዚሁ ዓላማ የተገነባው ትምህርት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በቅንጅት መሰራቱንም አመልክተዋል።

የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደመላሽ ንጉሴ በበኩላቸው በ'ቦባ ቆጫ' ቀበሌ የተገነባው ትምህርት ቤት የነገውን ትውልድ ህይወት ለማሻሻል ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል።

በቀጣይ የአካባቢውን ተወላጆችና ኅብረተሰቡን በማስተባበር መሰል የትምህርት ቤት ግንባታ ሥራን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ትምህርት ቤቱ ከ650 በላይ ተማሪዎችን መቀበል የሚያስችል አቅም እንዳለውም በወቅቱ ተገልጿል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top