ስለ ፍትሕ ሲባል

7 Mons Ago 802
ስለ ፍትሕ ሲባል

ነገር በምሳሌ ነውና በዚህች በአንድ ወቅት በሰማኋት ጨዋታ የዛሬውን የሕግ ጉዳይ እንጀምር።

አንዲት ላም ባቅራቢያዋ ካለ ጫካ ውስጥ ልቧ እስኪጠፋ እየሮጠች ስትሸሽ መንገድ ላይ ከዝሆን ጋራ ይገጣጠማሉ።

አያ ዝሆን ጠየቀ ‘‘ምነው ላሜ ቦራ በሰላም ነው እንዲህ ምትፈረጥጭው?’’

ላሜ ቦራ እያለከለከችና በፍርሀት ወደኋላዋ እየተገላመጠች ‘‘ኧረ ጉድ ፈልቷል! በጫካው ያሉ ጎሾች ሁሉ እንዲያዙ ታዟል።’’ አለችው

ዝሆንም ጠየቃት

‘‘ታዲያ አንቺ ላም እኮ ነሽ ምንድን ነው እንዲህ ሚያስሮጥሽ?’’

ላሜ ቦራ መለሰች "ላም መሆኔንማ አላጣሁትም። ድንገት ጎሽ ናት ብለው ቢይዙኝ ግን ላም እንጂ ጎሽ አለመሆኔን ለማረጋገጥ ብዙ ዓመታትን ይፈጃል ብዬ እኮ ነው!’’ ስትለው ዝሆኑም ከላሟ ጋር አብሮ በሩጫ መሸሽ ጀመረ።

ይህቺ ጨዋታ በአዝጋሚና ተአማኒነት ያጣ የዳኝነት ሥርዓት ውስጥ ንፁሀን የሚከፍሉትን ከባድ ዋጋ የምትጠቁም ስላቅ ነች። የሀገርህ የፍትሕ ሥርዓት ላይ መተማመን ካልቻልክ ባታጠፋም ደንጋጣ ነህ።

"ነፃና ገለልተኛ በጕልበት፣ በስልጣን፣ በገንዘብ፣ በወገንተኝነት ተፅዕኖ የፍትሕ ሚዛንን የማያዛባ ዳኛ አለ!" ብለህ ካላመንክ ጉዳይህን ወደ ፍርድ አደባባይ ለማምጣት ትፈራለህ። ከዚህ ስጋት እንድንላቀቅ የወጡት ሕጎች ምን ይላሉ ሚለውን እንይ።

የዳኘት ነፃነት

በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌደራሉም ሆነ የክልል ፍርድ ቤቶች ከማንም ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው እንዲሰሩ ተቋማዊ ነፃነታቸው በሕገ መንግስታችን አንቀፅ 78 ስር ተረጋግጧል።

 ‘‘ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት ያከናውናሉ። ከሕግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ አይመሩም።’’ተብሎ በአንቀፅ 79(3) ስር ሕገ-መንግስታዊ መብትና ግዴታ ወንበሮቻችን (ዳኞቻችን) ላይ የተጣለባቸው ማንኛውንም ለዳኝነት የሚቀርብላቸው ጉዳይ ላይ በሚከተሉት ሥነ-ሥርዓትና በሚተረጉሙት ሕግ ላይ እንደ አንድ ዜጋ ወይም እንደ ተሟጋች መተማመኛ እንዲኖረን ነው።

ፍትሕ (ዳኝነት) የማግኘት መብት

ማንኛውም ዜጋ በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ በፍርድ ቤት ወይም በሕግ የመዳኘት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብቱ በሕገ መንግስታችን አንቀፅ 37(1) ስር ተጠብቆለታል።

እነዚህ ሕገመንግስታዊ ድንጋጌዎች በቀልዱ ላይ ላሟና ዝሆኑ እንዳረጉት የተንዛዛ መዘግየት የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ስለሚቆጠር) የሚያስከትለውን መጉላላትና ልፋት በመፍራት ሽሽት እንዳይከሰት መተማመኛ ይሆኑ ዘንድ  የተገቡ ቃል ኪዳኖች ናቸው።

በሕገ መንግስቱ መሰረት የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ መተማመን እንዲኖረን ፍርድ ቤቶቻችን ከተቋማዊ አደረጃጀታቸው አንስቶ እስከ ዳኞች አሿሿም ድረስ ነፃነታቸውንና ገለልተኛነታቸውን በማስጠበቅ ጠንካራና እራሳቸውንም አስከብረው ሕጉንም የሚያስከብሩ መሆን አለባቸው።

ሌሎች የፍትሕ ሥርዓቱ አካላትስ

የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ዜጎች አመኔታ እንዲኖረን ሌሎች የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት ዓቃቢ ሕግ እና ፖሊስ እንዲሁም ማረሚያ ቤት የተጣለባቸውን ግዴታዎች በሕግ አግባብ መወጣት አለባቸው።

ከነኚህ የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት በተጨማሪም እያንዳንዱ ዜጋ ፍትሕን በሚሻበት ጉዳይ ላይ ሁሉ ዳኝነት የማግኘት መብቱን ተጠቅሞ እስከ መጨረሻው የዳኝነት አካል በመድረስ ለፍትሕ ሥርዓቱ መዳበር አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበታል። ምክንያቱም ያለ ተቋማት ቁርጠኝነትና የሕዝብ ንቁ ተሳትፎ የቱንም ያህል ሕጎች ቢወጡ ዜጎች ሕግ ተከብሯል፣ ፍትሕ ሰፍኗል፣ የሌላውን መብት አከብራለሁ፣ መብቴንም በሕግና በዳኝነት አስከብራለሁ ብለው የሚተማመኑበት የፍትሕ ሥርዓት ሊኖር አይችልም።

በምንሰማው ነገር ፈርተን ከሕግ አካላት ከሸሽን ወይም መብታችንን ከማስከበር ተቆጥበን ከተቀመጥን አመኔታ ያጣንበት የፍትሕ ሥርዓት በሚያገለግላቸው ዜጎች ንቁ ተሳትፎ ሳይፈተሽና ሳይጋለጥ ተገቢውን ማስተካከያ እንዲደረግበት ለሚመለከታቸው አካላት ባግባቡ ሳይደርስ ጠቅላላው ሕዝብም ግድፈቱን ዓይቶ ቅሬታውን ሳይገልፅበት ተሸፋፍኖ እንዲቀርና እየባሰበት እንዲሄድ እገዛ እንደማድረግ ይቆጠራል።

እንደ አንድ ዜጋ ምን ይጠበቅብናል:-

ፍትሕ ከማግኘትና ሕግን ከማስከበር ጋር በተያያዘ የምናውቀውን መረጃ ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ፣ ሕገወጥ ድርጊቶችን በማጋለጥና ለፍርድ እንዲቀርቡ በማድረግ እያንዳንዳችን እንደዜጋ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የፍትሕ ሥርዓታችን እንዲዳብር እና እንዲሻሻል ማገዝ እንችላለን።

ይህ ደግሞ በዚህ ዘመን ቀላል ሆኗል። በእጃችን ባለው የስልካችን ካሜራና በተለየያዩ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ሀሳብ መለዋወጫ መንገዶች ሕገወጥ ተግባራትን ማጋለጥና የሕግ አካላት ያን ግብአት አድርገው ሕግን እንዲያስከብሩ፣ ተጠርጣሪዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡና ተበዳዮች እንዲካሱ የበኩላችንን ማድረግ እንችላለን።

ለዚህ አብነትም በማህበራዊ ሚዲያው አማካኝነት በቅርብ ጊዜያት ትኩረት እንዲያገኙ የተደረጉ ሕገወጥ ተግባራትን መጥቀስ እንችላለን። አንዳንድ ሕግ አስከባሪዎች የሚፈፅሙት የሰብአዊ መብት ጥሰትን፣ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሀሰትና ሕዝብን የሚያሸብር መረጃ የሚለቁ ግለሰቦችን፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻን፣ ጠለፋን፣ የተሰረቁ ተሽከርካሪዎችን መጠቆምን፣ በወንጀል ተጠርጥረው የተሰወሩ ሰዎችን መጠቆምና  የአንዳንድ ተቋማትን ብልሹ አሠራር የማጋለጥ ተግባራት ዜጎች በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በመጠቀም ፍትሕን ለማስፈን እና ሕግን ለማስከበር ያበረከቱት አስተዋፅዎች ይገኙበታል።

በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የማይተማመን ባለጉዳይ በሕግ የሚገባውን መብቱን እንኳን በጉቦ ወይም በምልጃ ለማግኘት ይሞክራል። የማይገባውንም በስልጣን፣ በጉቦ ወይም በሌላ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለማግኘት የሚሞክረውም ቢሆን በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ አመኔታ ያጣ ሰው ነው። የፍትሕ ሥርዓቱ የራሱ ችግር ስላለበት የኔን ችግር አይደርስበትም ቢደርስበትም በእጅም በእግርም ብዬ አስቆመዋለው ብሎ ስለሚያምንም ይሄን ክፍተት ለግሉ መጠቀሚያ ማድረግ ይፈልጋል። 

የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለው አመኔታ የሚያድገው በፍትሕ ተቋማቱ ነፃና ገለልተኛ ፍትሕ ሲሰጥና ይህም ለሕዝቡ ግልፅ ሲሆን ነው። በተጨማሪም አግባብ ባለው ጊዜ የወንጀልም ሆነ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ውሳኔ ማግኘት ሲችሉ ነው። የህብረተሰቡን አስተያየትና ጥቆማዎች በመቀበልም ተቋማቱ አሠራራቸውን ግልፅና ተጠያቂነት የሰፈነበት፣ አገልግሎታቸውን ደግሞ ቀልጣፋና ዘመናዊ ማድረግ ሲችሉ ነው።

ከኛ ከሁላችንስ ምን ይጠበቃል? ለፍትሕ ቀናኢ መሆን! ማለትም በኛም ሆነ በሌሎች ላይ ሕገ ወጥ ተግባራት ሲፈፀሙ ሕጋዊ እርምት እንዲወሰድ ከሚመለከተው አካል ጋር መተባበር፣ መብትን እና ግዴታን አውቆ የፍትሕ ጉዳይ የኔም ጉዳይ ነው ማለት ይጠበቅብናል።

ከፍትሕ ሥርዓቱ ተቋማዊ ቁርጠኝነት በማይተናነስ መልኩ እያንዳንዱ ባለጉዳይ መጉላላትን ወይም የፍትሕ መዛባትን ፈርቶ ከመሸሽ ይልቅ ያሉትን ችግሮች በተጨባጭ በማጋለጥና እንዲቀረፉ የየበኩሉን በማገዝ ያገባኛል ማለት አለበት። አልያ እስኪጣራ ከምጉላላ ብሎ እንደ ላሟና ዝሆኑ መሸሽ የፍትሕ ሥርዓቱን የባሰ እንዲዳከምና ችግሩ እንዲባባስ ማድረግ ይሆናል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top