የጣልያኗ ቬነስ የተመሰረተችው ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፤ ከተማዋ በመካከለኛው ዘመን የትልቅ የባህር ኃይል ባለቤት መሆን ችላ ነበር። በአድሪያቲክ ባህር ውስጥ ያለው ስልታዊ አቀማመጧ በአውሮፓ እና በምስራቅ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ እንድትቆጣጠር አስችሏታል። ከተማዋ በንግድ በተለይም በቅመማ ቅመም፣ በሐር እና በቅንጦት ዕቃዎች ትታወቃለች።
ቬነስ በአስደናቂ እና ውብ ስነ-ሕንፃዋ ትታወቃለች። ከተማዋ እንደ ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል፣ የዶጌ ቤተ መንግሥት እና የሪያልቶ ድልድይን በመሳሰሉ ቅርሶች ያጌጠች ናት።
የከተማዋ ሰፊ የንግድ አውታሮች እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች በሜዲትራኒያን አካባቢ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንድታሳድር አስችሏታል።
ቬነስ በባህላዊ እና ጥበባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ሚና ተጫውታለች። እነዚህ ታሪካዊ እውነታዎች የቬነስን የጥበብ እና የባህል ማዕከልነት፣ በታሪኳ ወቅት ያሳየችውን አስደናቂ ዕድገት እና ተፅዕኖ ያጎላሉ።
ቬነስ በውስብስብ የቦይ እና የድልድይ ኔትወርኳ ትታወቃለች። ከእግር ጉዞ በተጨማሪ በከተማዋ ዋናው የመጓጓዣ ዘዴ ጀልባ ነው። “ጎንዶላስ” የከተማዋ ተምሳሌት የሆኑ የቬነስ ባህላዊ ጀልባዎች ናቸው። እነዚህ ጀልባዎች በዋናነት ለመጓጓዣ እና ለቱሪዝም ያገለግላሉ፤ በከተማዋ ውስጥ ወደ 400 የሚጠጉ ፈቃድ ያላቸው ጀልባዎች አሉ።
የቬነስ ከተማ ሐይቆቿን ጨምሮ በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ እውቅና አግኝተዋል። ከተማዋ በሚያማምሩ ቤተመንግሥቶች እና ሕንፃዎች የተሞላች በመሆኗ፣ በውሃ ላይ የተገነባች ድንቅ ከተማ ምሳሌ ተደርጋም ትወሰዳላች። ቬነስ ለዘመናት በዘለቀው የመስታወት አሰራር በተለይም በሙራኖ ደሴቷ ትታወቃለች።
በቬነስ ከተማ በሕዝብ አደባባዮች እርግቦችን መመገብ በሕግ የተከለከለ ሲሆን፤ ይህ ሕግ የከተማዋን ንፅህና ለመጠበቅ ያለመ ነው፤ ይህ ብቻም አይደለም፣ በቬነስ ቦይ ውስጥ መዋኘት የተከለከለ ነው። ይህም የህዝብን ደህንነት ለማረጋገጥ እና የቬነስ መሠረተ ልማት ወሳኝ አካል የሆኑትን ቦዮቹን ለመጠበቅ ነው።
በከተማዋ ሐውልቶች ወይም በታሪካዊ ቦታዎች ላይ መቀመጥ፣ መቆም ወይም መውጣት በጥብቅ የተከለከለ ነው። ይህ ሕግ ባህላዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ እና በእነዚህ አስፈላጊ ምልክቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል እንደሆነም ይነገራል። እነዚህ ሕጎች የቬነስን ውበት፣ ታሪክ እና ልዩ አካባቢ ለመጠበቅ ይተገበራሉ።
ሌላኛው አስገራሚው ነገር ደግሞ በቬነስ ታሪካዊ ማዕከል ውስጥ ብስክሌት መንዳት አይፈቀድም። ምክንያቱም ጎብኚዎች ከተማዋን በእግር ወይም በጀልባ እንዲጎበኙ ለማበረታታት ነው።
በሌላ በኩል በከተማዋ በደረጃዎች፣ በድልድዮች ወይም በሕዝብ አደባባዮች ላይ መቀመጥ የተከለከለ ተግባር ነው። ይህ ሕግ የእግረኛ ትራፊክ ፍሰትን ለመቆጣር እና በተጨናነቁ አካባቢዎች አደጋ እንዳይፈጠር ለመከላከል ያለመ ነው።
በቬነስ ባለቤት የሌላቸውን እንስሳት በሕዝብ አደባባዮች መመገብ በሕግ የተከለከለ ነው። ይህ ሕግ በከተማዋ ባለቤት የሌላቸው እንስሳት እንዳይበራከቱ እና ከተማዋን እንዳያቆሽሹ ለመከላከል የተደነገገ ነው።
ቬነስን ለመጎብኘት ሲያስቡ እነዚህን ሕጎች ማወቅ እና ማክበር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው።
በተስሊም ሙሀመድ