- "ሀገር በቀል ዕውቀቶች ችላ ተብለዋል" የሚለው ሃሳብ ልክ አይደለም፡- ዶ/ር ጌታቸው አዲስ
- ሀገር በቀል ዕውቀቶች እንዳያድጉ የምዕራባውያን ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡- የባህላዊ ሐኪም
***************
በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ያሉ ነባር ሀገር በቀል ዕውቀቶች እንዳያድጉ የምዕራባውያን ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ፀሐፊ እና የባህላዊ ሃኪም የሆኑት በቀለች ቶላ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ገልፀዋል፡፡
ኢኮኖሚው፣ ቴክኖሎጂው፣ የትምህርት ስርዓቱ፣ የጥበብ ሙያ እና አንዳንድ ነገሮች በምዕራባውያን ተፅዕኖ ስር መሆናቸው ያለንን እንዳናሳድግ እንደ ማነቆ ተጋርጠዋል ይላሉ በቀለች ቶላ፡፡
የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና ለአብነትም ጤፍ በነባር እውቀት እንደሚለማ ያነሱት ባለሙያዋ፤ ይህን በዕውቀት፣ በሳይንስ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ለማዘመን የእነርሱ ተፅዕኖ መኖሩን ያነሳሉ፡፡
በሌላ በኩል ትኩረት ተሰጥቶት በሀገሪቱ የትምህርት ስርዓቱ ውስጥ በማካተት ተማሪዎች ስለ ጤፍ እንዲያውቁ አለመሞከሩን የሚተቹት ፀሐፊ እና ባህላዊ ሐኪሟ፤ በሚገባው መጠን ተጠቃሚ ልንሆን ያልቻልነው ለዚህ ነው ይላሉ፡፡
ሌሎችም ሀገር በቀል ዕውቀቶች በሳይንሱ ብሎም በቴክኖሎጂ ሳይደገፉ አሁን ላይ ሀገርን እየመገቡ እና ኢኮኖሚውን እየደገፉ እንደሚገኙ ያነሳሉ፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የሚኖሩ ህዝቦች ከእንቅልፋቸው መንቃት እና ያላቸውን ገፀ-በረከት መመልከት አለባቸው ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
ከትላንት እስከ ዛሬ ሀገር እያገዙ ያሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለማጎልበት ኃላፊነቱ ወደ አንድ ወገን የማይገፋ በመሆኑ ሁላችንም በአንድነት እነዚህ ሀብቶቻችንን ለማወቅ መጣር አለብን ይላሉ፡፡
ኢቢሲ ሳይበር የሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለመረዳት ወጣቱ ምን ያህል ፍላጎት አለው ሲል በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሕግ ተማሪ የሆነችውን ኤደን አቡቸርን አነጋግሯል፡፡
ኤደን ወጣቱ የሀገሩ የሆኑ ነገሮችን ለማወቅ እና ለመጠቀም ያለው ተነሳሽነት ከፍተኛ ቢሆንም፤ ሁኔታዎች ግን ምቹ አይደሉም ትላለች፡፡
የትምህርት መፅሐፎቻችን ያሉንን ነገሮች በቅንጭብ እንጂ በበቂ የሚያሳዩ ባለመሆናቸው፤ በትምህርት ቤት ቆይታችን ስለ ሀገር በቀል ዕውቀቶቻችን ማወቅ በሚገባን መጠን ሳናውቅ እንወጣለን ስትል ትናገራለች፡፡
ለመጪው ትውልድ በሚገባ ታስቦ እና ታቅዶ እነዚህን ሀገር በቀል ዕውቀቶች እንዲያውቁ የሚቻልበት መንገድ ቢፈጠር መልካም ነው ስትል ታነሳለች፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ በአርማወር ሀንሰን ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ጌታቸው አዲስ፤ ሀገራችን ካለፈው ዘመን ቁሳዊ እና መንፈሳዊ የሆኑ ቅርሶችን ተረክባ በጊዜ ሂደት ጠቃሚ የሆኑትን አጥልላ እየተጠቀመችበት ትገኛለች ይላሉ፡፡
“ሀገር በቀል ዕውቀቶች ችላ ተብለዋል” የሚለው ሃሳብ ልክ አይደለም ሲሉም ነው የሚገልጹት፡፡
በመንግስት በኩል የሀገር በቀል ዕውቀቶችን ከግንዛቤ በማስገባት የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብዝኀ-ሕይወት ኢንስቲትዩት፣ አርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን፣ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም የዩንቨርስቲ ዲፓርትመንቶች እየሰሩበት እንደሚገኙም ነው ያብራሩት፡፡
ተቋማቱ ለተሻለ ውጤታማነት መቀናጀት አለባቸው የሚሉት ዶ/ር ጌታቸው፤ ባህላዊ የሆኑ "ሀገር በቀል ዕውቀቶቻችን ችላ ተብለዋል" የሚለው ሳይሆን በሚፈለገው መጠን በዘመናዊነት ለመደገፍ አልተሞከረም የሚለው ሃሳብ እንደሚያስማማ ይናገራሉ፡፡
ይህን መሰል ዕውቀት ከታች ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ ወደ ውጤታማነት እንደሚያደርስ ገልጸው፤ በዚህ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶች እንዳሉ እሙን ነው ብለዋል፡፡
ሆኖም ግን እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት የተለያዩ ሙከራዎች፣ ምርምሮች እንዲሁም በዩንቨርስቲዎች ጥናቶች እየተደረጉ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
በአፎሚያ ክበበው