የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማዘመን ከአዘርባጃኑ ጉብኝት ትልቅ ተሞክሮ ተገኝቷል፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

8 Mons Ago 720
የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማዘመን ከአዘርባጃኑ ጉብኝት ትልቅ ተሞክሮ ተገኝቷል፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
በኢትዮጵያ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከአዘርባጃኑ ጉብኝት ትልቅ ተሞክሮ መገኘቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
 
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው እለት በአዘርባጃን ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 
በማብራሪያቸውም በአዘርባጃን በተለይ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል እየተሰጠ እንደሚገኝና ይህም የአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋና ምቹ እንዲሆን ማድረጉን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
 
የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ የሆነ ሪፎርም ማድረጉን ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ደግሞ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ሪፎርም የማድረግ ስራዎች ተጀምረዋል ብለዋል።
 
የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ስራ እየተካሄደ በመሆኑ በዚህ ረገድ ከአዘርባጃን ጋር በመስራት በዘርፉ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ጉብኝቱ እንደሚጠቅምም አክለዋል።
 
በተለይ በስምንት የመንግስት ተቋማት ውስጥ አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸው ከአዘርባጃን የተገኘው ተሞክሮ ለተጀመረው ስራ እንደ ግብዓት እንደሚያገለግል መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
የኢትዮጵያና የአዘርባጃን የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውንም ጠቁመዋል።
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top