በየቀኑ ሕይወቱን ለማቆየት የሰውን ደም የሚጠብቅ ሰው አለ፦ የኢትዮጵያ ሂሞፊሊያ ማኅበር አባል እና የሂሞፊሊያ በሽታ ተጠቂ
**********************
በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሌላ ሰው ደም ይፈልጋሉ፡፡ አንዳንዶቹ በቀዶ ጥገና ጊዜ የሚፈልጉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ከአደጋ በኋላ ወይም የውስጥ ደዌ ችግር ኖሮባቸው ደም ወይም የተወሰኑ የደም ሴሎችን በሚፈልጉበት ወቅት ነው፡፡
ናትናኤል ገመቹ ይባላል ወደዚች ምድር ከተቀላቀለበት ከሰባተኛ ቀኑ ጀምሮ አሁን እስካለበት ጊዜ ከደምጋር ቁርኝት ያለው ወጣት ነው፡፡
ገና በተወለደ በሰባተኛው ቀን ነበር "ሂሞፊሊያ B" የተባለ በሽታ እንዳለበት የታወቀው፤ በግርዛት ወቅት ላይ ከፍተኛ ደም መፍሰስ አጋጥሞት እንደነበር የሚገልጸው ወጣት ናትናኤል፤ በወቅቱ ከወላጅ እናቱ ደም በማግኘቱ መትረፍ መቻሉን ከኢቢሲ ሳይበር ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል፡፡
ከተወለደ ከሰባተኛው ቀን ጀምሮ ለ29 ዓመታት በለጋሾች ደም ነፍሱን ያቆየው ናትናኤል፤ ከአራት ዓመቱ ጀምሮ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል ስለማድረጉ ይናገራል፡፡
ውልደቱ እና እድገቱ በሻሸመኔ የሆነው ይህ ወጣት ከህጻንነት ዕድሜው ጀምሮ ነበር ደም ለመውሰድ እና ሕክምናውን ለመከታተል ከሻሸመኔ አዲስ አበባ ይመላለስ የነበረው፤ በደም እጦት ምክንያትም ከባድ የሆኑ ችግሮችን እንዳስተናገደም ይናገራል፡፡ በዚህ ምክንያት ቤተሰቦቹም ጭምር ብዙ አስከፊ ጊዜያት እንዳሳለፉ ያስታውሳል፡፡
በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ደም መለገስ ከባድ ተደርጎ እንደሚታይ የሚገልጸው ወጣቱ፤ ይህም ለታማሚዎች ፈተና መሆኑን ይናገራል፡፡
በየዕለቱ ነፍሱን ለማቆየት ከለጋሾች ደም የሚጠብቅ አለ የሚለው ወጣት ናትናኤል፤ ህብረተሰቡ ይህን ተገንዝቦ ደም እንዲለግስም ይማፀናል፡፡
አንድ ሰው አንድ ጊዜ ደም ሲለግስ የሦስት ሰዎች ሕይወትን ከሞት ይታደጋል ሲልም ይገልፃል፡፡
ከዚህም አልፎ ደም መለገስ ጤንነትን መጠበቅ በመሆኑ ፤ ህብረተሰቡ ደም መለገስን ባህል ሊያደርግ ይገባል ሲልም ተናግሯል፡፡
ከደም አቅርቦት እና እጥረትጋር ተያይዞ ኢቢሲ ሳይበር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ደም እና ኅብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው ከፆም እና ከበዓል ጋር ተያይዞ በሚያዝያ ወር መጨረሻ ሳምንት ጀምሮ ይሰበሰባል ተብሎ ከታሰበው ደም አንጻር እጥረት መግጠሙን ተናግረዋል፡፡
የፆሙን ወቅት ተክትሎ የደም እጥረት መፈጠሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ህብረተሰቡ ደም እንዲለግስ እና የዜጎችን ሕይወት እንዲታደግልን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ደም እና የደም ተዋፅኦዎች ዘመናዊ በሚባለው ሕክምና ውስጥ ዋነኛ ግብዓት ናቸው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም ከወሊድ ጋር ተያይዞ ደም ለሚፈሳቸው እናቶች፣ በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ደም ለሚፈሳቸው ታማሚዎች፣ ሲወለዱ ጀምሮ የደም ማነስ ላለባቸው ህፃናት፣ ለካንሰር ታማሚዎች የደም ሕክምና በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡
በአንድ ሀገር ሁኔታ በዓመት አንድ በመቶ የሚሆነውን የህዝቡን ቁጥር ያህል ደም ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ስሌት ኢትዮጵያም በየዓመቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዩኒት ደም እንደሚያስፈልጋት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
እየተሰበሰበ ያለው የደም መጠን ግን በወር ከሚያስፈልገው 100 ሺህ ደም ዩኒት ጋር የማይመጣጠን እና 28 ሺህ ዩኒት ገደማ ብቻ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እስካሁን ከለጋሾች በተበረከተ ደም የብዙዎች ነፍስን ማስቀጠል ተችሏል፡፡ ነገር ግን ልክ አንደ ናትናኤል ያሉ ዜጎችን ለመታደግ አዘውትረው ደም የሚፈልጉ በርካቶች ናቸውና ደም መለገስ የሁል ጊዜ ተግባር መሆን ይኖርበታል ፡፡
ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን እንዲያዳብር የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ደም በበጎ ፍቃደኝንት የሚሰጥ አገልግሎት መሆኑን በመረዳት ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉን እንዲያዳብር ጠይቀዋል፡፡
በተስሊም ሙሀመድ