የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ አውደ ርዕይ ተካሄደ

8 Mons Ago 632
የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ አውደ ርዕይ ተካሄደ
የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ የተዘጋጀ አውደ ርዕይ አዲስ አበባ በሚገኘው የሕብረቱ ዋና መስሪያ ቤት ዛሬ ተካሂዷል።
 
በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፣ የሕብረቱ የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት የግንቦት ወር 2024 ሊቀ-መንበር አምባሳደር ኢኖሰንት ሺዮ፣ የሕብረቱ ኮሚሽነሮች፣ የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ እርዳታና የልማት አጋር ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።
 
አውደ ርዕዩ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽንና የልማት አጋሮች በአህጉሪቱ ያከናወኗቸውን የሰብዓዊ ስራዎችና የሰብዓዊ እርዳታ ምላሾች የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።
 
በተጨማሪም የአፍሪካ የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ግጭቶችን በመከላከል፣ ምላሽ በመስጠትና በመፍታት ያከናወኑት ተግባር በአውደ ርዕዩ ላይ ለዕይታ ቀርበዋል።
 
የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴና ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በአፍሪካ የሰሯቸውን የሰብዓዊ ዲፕሎማሲ ተግባራትን በአውደ ርዕዩ አስጎብኝተዋል።
 
አውደ ርዕዩ የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አስመልክቶ ካዘጋጀቻው መርሐ ግብሮች መካከል አንዱ ነው።
 
የምክር ቤቱ የ20ኛ ዓመት ምስረታ የተመለከቱ ዝግጅቶች እስከ እ.አ.አ 2024 ማብቂያ ድረስ እንደሚቀጥል ኢዜአ ዘግቧል።
 
የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት እ.አ.አ ግንቦት 25/2004 የተቋቋመ ሲሆን በአህጉሪቱ ግጭቶች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ መከላከል፣ የግጭት አስተዳደርና አፈታት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top