የዜጎችን የፍልሰት ምጣኔ ለመግታትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

8 Mons Ago 743
የዜጎችን የፍልሰት ምጣኔ ለመግታትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜጎችን የፍልሰት ምጣኔ ለመግታትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር ተፈራረመ።
 
ስምምነቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቢባቱ ዋንፎል ፈርመውታል።
 
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ስምምነቱን አስመልክቶ እንደገለጹት፤ በርካታ ዜጎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ተለያዩ ክፍለ ዓለማት በሕገ ወጥ መንገድ ይሸጋገራሉ።
 
ይህም ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ስደተኞች ኢትዮጵያን እንደ መሸጋገሪያ በመጠቀም ይተላለፋሉ ብለዋል።
 
በዚህም በርካታ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ የሌሎች አገራት ዜጎች ለእንግልትና ለተባባሰ ችግር እንደሚዳረጉ ጠቅሰዋል።
 
መንግስት በዚህ ረገድ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ችግሩን ለማቃለል በትኩረት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
 
ለዚህም በቅርቡ ይፋ የሚደረገው የአምስት ዓመት ዕቅድ አንዱና ዋነኛው ሲሆን ዕቅዱን በአግባቡ ለመፈጸም የአጋር አካላት ሚና ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
 
ከዓለም የፍልሰት ድርጅት ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ቀደም ሲል በቅንጅት የሚሰሩ ተግባራትን ለማጠናከርና ለቀጣዩ የአምስት ዓመት ዕቅድ አተገባበር የጎላ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
 
በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቢባቱ ዋኔ-ፎል በበኩላቸው፤በየትኛውም ሀገራት የሚገኙ ሰዎች ሕገ-ወጥ ስደትን እንደ አማራጭ መውሰድ መጀመራቸውን ጥናቶች ማመላከታቸውን ገልጸዋል።
 
በተለይም ለመሸጋገሪያነት አመቺ ናቸው ተብለው በሚታመኑ ሀገራት የፍልሰተኞች ቁጥር እንደሚጨምር ጠቁመው በዚህም ስደተኞች ለተባባሰ ችግር የሚዳረጉባቸው ዕድሎች ሰፊ መሆናቸውን አክለዋል።
 
በመሆኑም በፍልሰትና የስደተኞች ደህንነት ማረጋገጥ ላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በርብርብ በመስራት ጉዳቱን መግታትና ማስቆም ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ችግሩን ለማቃለል የሚከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ድርጅታቸው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top