የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል

14 Days Ago
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

“ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚያብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና ” ተብሎ በወንጌል እንደተጻፈው የአዳም ዘር ሥርየትን ያገኝ ዘንድ አምላክ አንድያ ልጁን መከራን ሊቀበል፣ ነፍሱን ስለብዙዎቹ ቤዛ ሊሰጥ እንደላከው መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡

ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሦሥት ቀንና ሦሥት ሌሊት እንደነበረ ሁሉ የሠው ልጅም በምድር ልብ ውስጥ ሦሥት ቀንና ሦሥት ሌሊትን አሳልፎ በትንሣዔ የመነሳቱን ትንቢት በምሳሌ እየገለፀ የሠው ልጅም በገሊላ ሳለ በኃጥያተኞች እጅ ተላልፎ ሊሰጥ እና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ሊነሳ ግድ ስለመሆኑ አስቀድሞ የማያልፍ ቃሉን ሰጥቷል፡፡

እንደቃሉም አንዱ ስለብዙዎች ቤዛ ሆኖ ሞትንም ድል አድርጎ በትንሣዔ ተነስቷል፡፡ ለእኛም ለሠው ልጆች ፍቅርን፣ እርስ በርስ መዋደድን፣ ለሠላምና ለነፃነት ራስን መስዋዕት መሆንን ቤዛና አብነት ሆኖ አሳይቶናል።

የ2016 ዓ.ም የትንሣዔ በዓልን ስናከብር በታላቁ መጽሐፍ እንደታዘዝነው ሁሉ ልቦቻችንን ለምህረት፣ሐይቅርታና ለእርቅና ከፍተን እና በልዩ ልዩ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን ለማገዝ እጆቻችንን ለድጋፍ በመዘርጋት፣ አንደበታችንንና ተግባራችንን በአገር ግንባታና ሠላም ማስፈን ላይ ሊሆን እንደሚገባ እያስታወስን ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ሁሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሣዔው በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴንን በታላቅ አክብሮት እገልፃለሁ ።

መልካም በዓል ይሁንልን!


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top