ሃማስ በግብፅ እና ኳታር የቀረበውን የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት ሃሳብ እንደሚቀል በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የሃማስ ቡድኑ መሪ ኢስማኢል ሃኒዬ የተኩስ አቁም ስምምነት ሃሳቡን መቀበላቸውን ለኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እና ለግብፅ የደህንነት ኃላፊ ማሳወቃቸው ተገልጿል።
በሃማስ ተቀባይነት ያገኘው የተኩስ አቁም ስምምነት ሃሳብ ምን አይነት ዝርዝር ጉዳዮች እንዳሉት ለጊዜው አለመገለፁን ሮይተርስ ዘግቧል።
በግብጽ የሚገኙ አሸማጋዮች በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ እና በሐማስ የተያዙ ታጋቾችን ለማስፈታት ያለመ የሁለት ቀናት ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ውይይቱ እሑድ መጠናቀቁን ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው ሐማስ የልዑካን ቡድኑ ከካይሮ ወደ ኳታር በማቅናት ከአመራሮቹ ጋር እንደሚመክር አስታውቆ እንደነበር ተጠቁሟል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ታጋቾች እንዲፈቱ፤ ለ40 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና በእስራኤል እስር ቤቶች የሚገኙ በርካታ የፍልስጤም እስረኞችን መፍታትን ያካተተ ሊሆን እንደሚችል ሲዘገብ ነበር።