የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይ ምክክር ተካሄደ

11 Days Ago
የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይ ምክክር ተካሄደ
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በፌደራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
 
በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔና ምክትል አፈጉበዔ፣ የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ የኮሚቴ አባላት፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች፣ የዲሞክራስ ተቋማት ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
 
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ቁርሾዎች እንዲጠገኑ እንዲሁም ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር እንዲሳካ የተሟላ የሽግግር ፍትሕ መተግበር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመድረኩ ገልጸዋል።
 
አስተዳደራዊ ፍትሕ ከወንጀል እና ፍትሐ ብሔራዊ ክርክሮች በላይ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ወይም እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር የፍትሕ ዘርፍ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
 
ምክር ቤቱ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚሰጠው የድጋፍ፣ የቁጥጥር እና የክትትል ዓይነቶችን ለመለየት ያስችለው ዘንድ በአዋጁ ዙሪያ ውይይት መደረጉ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመላክተዋል።
 
የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ የፌደራል ሥነ-ሥርዓት አዋጅ አፈፃፀምን በተመለከተ በአዋጁ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ከመወጣት ጎን ለጎን በአዋጁ ተፈፃሚነት ላይ የክትትል ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
 
ተቋሙ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን አዘጋጅቶ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ቀርቦ መጽደቁንም አመላክተዋል።
 
አያይዘውም አዋጁ እና ፖሊሲው በመንግስት አካላት ዘንድ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር እንዲሁም ተቋሙ በትግበራ ሂደት የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ምክር ቤቱ የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ ያግዘው ዘንድ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።
 
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ይዘት እና ዳሰሳ፣ አስፈላጊነት፣ የሽግግር ፍትሕ ዓላማ እና መርሆዎች እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በሚኒስትሩ ቀርበዋል።
 
ከግጭት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ በሚደረግ ሽግግር፣ ከሽግግሩ በፊት በደረሱ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች የተሟላ መፍትሄ ለመስጠት የሽግግር ፍትህ አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትሩ አክለው ተናግረዋል።
 
በውይይት መድረኩ የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎችን የሚያመላክቱ በርካታ ሃሳብ እና አስተያየቶች መነሳታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top