የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ መንገድ ለመተግበር የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የማይተካ ሚና እንዳለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ ገለጹ።
አፈ-ጉባኤው ይህንን ያሉት፤በፍትሕ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅና በሽግግር ፍትሕ ፓሊሲ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ነው።
አስተዳደራዊ ፍትሕ የማኅበራዊ ፍትሕ የማዕዘን ድንጋይ ነውም ሲሉ አፈ-ጉባኤው ገልጸዋል።
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ባማከለ መንገድ የተዘጋጀ እና በመላ ሀገሪቱ ግብዓት ተሰብስቦበት የተዘጋጀ ፓሊሲ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የምክክር መድረኩን አላማ ካስተዋወቁ በኋላ፤ አፈ -ጉባኤ ታገሠ ጫፎ በፖሊሲውና ሥነ-ስርዓት አዋጁ የተዘጋጀውን የምክክር መድረክ በይፋ አስጀምረዋል።
በውይይት መድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።