የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ እና በአፍሪካ ሕብረት የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ጃቬር ፔሬዝ በፈረንጆቹ ግንቦት 9 የሚከበረውን የአውሮፓ ቀን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በመግለጫቸው፤ ከ74 ዓመታት በፊት ጀምሮ የአውሮፓ ሕብረትን ለመመስረት በጥቂት የአውሮፓ ሀገራት መካከል የትብብር ስምምነት መደረጉን አስታውሰዋል።
የአውሮፓ ህብረት አሁን ላይ 27 ሀገራትን በፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥምረት ያቀፈ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የአውሮፓ ሕብረት የነፃ ፓስፖርት ዝውውርና የጋራ መገበያያ ገንዘብ የመጠቀም ትግበራን ጨምሮ በሀገራት መካከል ሁለንተናዊ ዘላቂ ትብብር የፈጠረበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ነፃነት፣ዴሞክራሲ፣ እኩልነትና ሰላም የማስፈን መርሆዎች እንዳሉት ጠቅሰው፤ የሕብረቱ አባል ሀገራት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል።
ሕብረቱ ኢትዮጵያን ጨምር ከተለያዩ ሀገራት ጋር በዘላቂና መርህ መር አግባብ የትብብር ግንኙነቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ከሕብረቱ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ አጋር ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ በፖለቲካና ኢኮኖሚ መስኮች ጠንካራ ትብብር መመስረታቸውን አንስተዋል።
ከኢኮኖሚና ንግድ ትብብር አኳያ ሕብረቱ በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ለማጎልበት የሚያስችሉ በርካታ ስምምነቶች ተግባራዊ ስለመደረጋቸውም ተናግረዋል።
በትምህርት፣ በጤና፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃና በስደተኞች ጉዳይ ላይም በትብብር እየሰሩ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
አውሮፓ 20 በመቶ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት መዳረሻ እንዲሁም ሁለተኛው የኢትዮጵያ ገቢ ምርቶች (ኢምፖርት) ምንጭ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል።
በአፍሪካ ሕብረት የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ጃቬር ፔሬዝ፤ የአውሮፓ ሕብረትና አፍሪካ በኢኮኖሚ፣ በሰላም መረጋጋት እንዲሁም በሰው ተኮር የልማት ስራዎች በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
በንግድና ኢንቨስትመንት ረገድም የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት ኩባንያዎች ከ241 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ኢንቨስትመንት እንዳላቸው መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በሰላምና መረጋጋት፣ በስደት እና በሌሎች የባለብዙ ወገን የትብብር መስኮችም በጋራ እየሰሩ ስለመሆኑ አንስተው፤ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።