ባለፉት 5 ዓመታት መንግስት ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሰርቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

1 Mon Ago
ባለፉት 5 ዓመታት መንግስት ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሰርቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

መንግስት ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን /ስታርት አፖችን/ በተሻለ ህግና የአሰራር ስርዓት ለመደገፍ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የ''ስታርት አፕ ኢትዮጵያ'' ፎረም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።

በመድረኩም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የግሉ ዘርፍ እንዲሁም ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ የሆኑ አብዛኛው የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መነሻቸው ስታርት አፕ መሆኑን ተናግረዋል።

ስታርት አፖች ከስራ ፈጠራ ባሻገር የማህበረሰቡን ችግሮች ከመሰረቱ የሚፈቱ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ካለው የህዝብ ቁጥር አንጻር አብዛኛው ወጣት መሆኑ ደግሞ ለስታርት አፕ ምቹ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በኢትዮጵያ ስታርት አፕ ብዙም ትኩረት እንዳልተሰጠው አስታውሰው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት መንግስት ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአይሲቲ ዘርፍ ከአምስቱ የብዝሃ ኢኮኖሚ አዕማዶች አንዱ ሆኖ በትኩረት እንዲሰራበት መደረጉ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን /ስታርት አፖችን/ ለማበረታታት የተወሰደ እርምጃ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ከለውጡ በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ስታርት አፖች ከ50 እንደማይበልጡ ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ከ900 በላይ ስታርት አፖች መኖራቸውን ተናግረዋል።

መንግስት በቀጣይ የስታርት አፕ ሀሳቦችን በተደራጀ ህግና አሰራር ሰርዓት ለመደገፍ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ከትንሽ ተነስቶ ወደ ትልቅ ኩባንያ የሚያድግ መሆኑን ወጣቶች ሊገነዘቡ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ወጣቶች የፈጠራ ሃሳባቸውን መውደድ፣ መቻል፣ መፈለግና መሸጥ እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

ጥልቅ ፍላጎት፣ ተልእኮ እና ችሎታ ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች መሳካት መሰረት መሆናቸውን አብራርተዋል።

የስራ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች ማደግ የሚችሉ በመሆናቸው ሀሳቦቻቸውን በአግባቡ ማውጣት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top