"በመዲናዋ ከማህበራዊ ትውስታ፣ ዘመናዊነትና መዝናኛነት ጋር በተገናኘ የቆዩ ቤቶች ሁሉ ቅርስ ሊሆኑ አይችሉም" - የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን

9 Mons Ago 1029
"በመዲናዋ ከማህበራዊ ትውስታ፣ ዘመናዊነትና መዝናኛነት ጋር በተገናኘ የቆዩ ቤቶች ሁሉ ቅርስ ሊሆኑ አይችሉም" - የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን

በአዲስ አበባ የመልሶ ግንባታና ኮሪደር ልማት የሀገር ሃብትና ቅርሶችን የመጠበቅ የመንከባከብና የመጠገን ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ።

በመዲናዋ የኮሪደር ልማት ሥራ ቅርሶችና መሰረተ ልማቶችን የመንከባከብ፣ የመጠበቅና የማደስ ሥራ በማከናወን በነበሩበት እንዲቀጥሉ መደረጉን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መግለፃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን ሃብትና ቅርሶች በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በመጠገን ለትውልድ እንዲተላለፉ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው።

የቅርስ ጥበቃና መስህቦችን የማስፋት ስራ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች እየተከናወነ ሲሆን በአዲስ አበባም ቅርሶችን የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የመጠገን ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በመዲናዋ የአራዳ፣ ጉለሌ፣ ቂርቆስ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች የአዲስ አበባ ቀደምት የምስረታ አካል በመሆናቸው የኪነ-ሕንፃና መልክዓ ከተማነትን የሚያሳዩ መታሰቢያዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም በመዲናዋ የቅርስ መስፈርቶችን ያላሟሉ ሁሉ የተመዘገቡ መኖራቸውን አስታውሰው ዓለም አቀፍ የቅርስ ምዝገባ ተሞክሮን መነሻ በማድረግ በተዘጋጀ መመሪያ መሰረት በአዲስ መልክ የቅርስ ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት ከዚህ በፊት የተመዘገቡ በቅርስነት የሚቀጥሉ ሲኖሩ በመመሪያው መሰረት መስፈርቱን የማያሟሉ ደግሞ አይቀጥሉም ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም በአዲስ አበባ የመልሶ ግንባታና ኮሪደር ልማት መጠበቅ ያለባቸው ቅርሶች እንዲጠበቁ መደረጉን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል።

በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ከማህበራዊ ትውስታ፣ ዘመናዊነትና መዝናኛነት ጋር በተገናኘ የቆዩ ቤቶች ሁሉ ቅርስ ሊሆኑ አይችሉም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከዚህ ቀደም መርካቶ የቃኘው ሻለቃ ሆቴል፣ ቤላ የነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ቤትና ፒያሳ የአድዋ ሆቴል የቅርስነት መስፈርት ሳያሟሉ ተመዝግበው እንደነበርም አስታውሰዋል።

በመሆኑም በመልሶ ግንባታና ኮሪደር ልማት ቅርሶች ተለይተው በቅርስ ምዝገባ መስፈርት ተመዝግበው እንዲጠበቁ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በየትኛውም ዓለም ልማትና ቅርስ ጥበቃ ሚዛኑን ጠብቆ እንደሚጓዝ ጠቁመው ቅርስ ጥበቃና ልማትን ማጣጣም ግዴታ ነው ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አስረድተዋል።

በመሆኑም የቅርስ ጥበቃና የልማት ስራዎች ተመጋግበው እንዲሄዱ በማድረግ የቅርስ መስፈርት የማያሟሉ ቤቶችንና አካባቢዎችን በመልሶ ልማት የቀደመ ስያሜና አገልግሎታቸው እንዲቀጥል ይደረጋል ነው ያሉት።

በኮሪደር ልማት ሥራው ቅርሶችና መሰረተ ልማቶችን የመንከባከብ፣ የመጠበቅና የማደስ ሥራ በማከናወን በነበሩበት እንዲቀጥሉ መደረጉን ከንቲባዋ መናገራቸው ይታወሳል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top