በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጀመሩት አበረታች ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ቋሚ ኮሚቴው አስገነዘበ

29 Days Ago
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጀመሩት አበረታች ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ቋሚ ኮሚቴው አስገነዘበ
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጀመሩት አበረታች ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገንዝቧል።
 
ቋሚ ኮሚቴው፤ በቦሌ አየር መንገድ ተዘዋውሮ የመስክ ምልከታ በማድረግ ከተቋሙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
 
የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ ፕሮፌሰር መሀመድ አህመድ አየር መንገዱን ለማስፋፋት እና ለማዘመን እየተሰሩ ያሉት በርካታ ፕሮጀክቶች የሚደነቁ መሆናቸውን እና ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
 
በክልል ከተሞች የሚገኙት የአየር መንገዱ መዳረሻዎችን መሰረተ ልማት የሟሟላት ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም የኮሚቴው ሰብሳቢ አሳስበዋል።
 
በሌላ በኩል አየር መንገዱ በቅርቡ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከመንገደኞች አገልግሎት አሠጣጥ ጋር በተያያዘ እየተነሱበት ላለው ቅሬታ መፍትሄ ለመስጠት፤ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልፀዋል።
 
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ስለ አየር መንገዱ አጠቃላይ ገፅታ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገለፃ አቅርበዋል።
 
ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወሩ ያሉ የተጓዦችን ቅሬታ ለመፍታት በማኔጅመንት በመወያየት የቅሬታ ማስተናገጃ ዴስክ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።
 
ብልሹ አሰራሮችን ለመቆጣጠር ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከኢሚግሬሽን ባለስልጣን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር እየተሰራ መሆኑንም አቶ መስፍን አክለዋል።
 
በቀጣይም አየር መንገዱ የደንበኞቹን ጥቆማ ተቀብሎ አስፈላጊውን ማስተካከያ የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
 
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ 5 ተጨማሪ የሀገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን ጨምሮ ቀደም ሲል የነበሩትንም የማዘመን ስራ እያከናወነ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።
 
አዲስ የሚገነቡትም ሚዛን ቴፒ አማን፣ነጌሌ ቦረና፣ያቤሎ፣ጎሬ መቱ እና ደብረ ማርቆስ መሆናቸውንና በቀጣዩ ዓመት ተጠናቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።
 
ይሁንና በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር፣ ለባለ ይዞታዎች ካሳ በመክፈል ቦታውን ነፃ አለማድረግ፣ ተቋራጮች በኮንትራት ውሉ መሰረት አለመሄድ እና የግንባታ ግብአቶች እጥረት ስራዎቹን ሊያጓትቱ እንደሚችሉ መናገራቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላታል።
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top