የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ለቡ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለልማት ከሚኖሩበት አካባቢ ለተነሱ ነዋሪዎች፣ ለአቅመ ደካሞች እና የሃገር ባለውለታዎች የሚሆኑ ሶስት ባለ አምስት ወለል የመኖሪያ ቤት ህንጻዎችን ግንባታ አስጀምረዋል::
ባለሃብቶችን በማስተባበር የሚገነቡት እነዚህ የመኖሪያ ቤቶች በ90 ቀናት ውስጥ ተጠናቅቀው ለነዋሪዎች እንደሚተላለፉ እና በአጠቃላይ 108 አባወራዎችን የቤት ባለቤት የሚያደርጉ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ "ከጎዶሏቸው በማካፈል ለዚህ በጎ ስራ እጃቸውን የዘረጉ ልበ ቀና ባለሃብቶችን በከተማችን ነዋሪዎች ስም ላመሰግናቸው እወዳለሁ" ብለዋል፡፡