በምስራቅ ጉጂ ዞን ሳባቦሩ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት ለመጠበቅ በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል።
የምስራቅ ጉጂ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቦጌ ታፈሰ ፤ የጉጂ ህዝብ በሰላም እና አንድነት ዙሪያ የተከበረ ባህልና ወግ እንዳለው ገልጸዋል።
ኃላፊው የህዝቡን ሰላምና ልማት ሲያውክ የነበረው የኦነግ ሸኔ ቡድን ተስፋ ቆርጦ እየተበታተነ እና በርካታ የቡድኑ ታጣቂዎች እጃቸውን እየሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የዞኑ ህዝብ ለበርካታ ጊዜያት በሽብር ቡድኑ ሲደርስበት የነበረውን በደል ለማስቆም ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር በጥምረት በመስራቱ ቡድኑ ለዞኑ ህዝብ ስጋት እንዳይሆን መደረጉን ነው የጠቀሱት።
በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ገልጸው፤ ህዝቡ ለሰላም ያለውን ፅኑ አቋም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በደቡብ ዕዝ የ42ኛ ክፍለጦር ዋና አዛዥ ተወካይ ሻለቃ ዑመር ዓደም በበኩላቸው፤
ሰላም ወዳዱ የጉጂ ህዝብ ለሰላም ትልቅ ቦታ ያለው በመሆኑ፤ በህብረተሰቡ ውስጥ ተሸሽገው የጠላትን እኩይ ሴራ የሚያስፈፅሙና የተለያየ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትን በማስተማርና ወደ ህዝቡ በመመለስ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቅርቡ ለሰራዊቱ እጁን የሰጠውና በሽብር ቡድኑ በኃላፊነት ሲሰራ የነበረው ገመዳ ዱጎ ወይም ሎንግ ፤ ቡድኑ እርስ በርሱም ቢሆን የማይግባባ የዘራፊዎች ስብስብ መሆኑን ገልጿል።
ኦነግ ሸኔ ያለምንም ዓላማ ህዝብን ሲበድል እንደነበር ያስገነዘበው የቀድሞው የሽብር ቡድኑ አመራር ፤ የቡድኑን ሴራዎች በማጋለጥና ህብረተሰቡን በማስተማር የሰላም ዘብ እንደሚሆን መናገሩን ከደቡብ ዕዝ የ205ኛ ኮር የሠራዊት ስነ ልቦና ግንባታ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የሳባቦሩ ወረዳ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአካባቢያቸው የነበረው የሰላም እጦት ያሳደረባቸውን ተፅዕኖ ተረድተው፤ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ለማስቀጠል የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በምክከር መድረኮቹ፤ የቡድኑን እኩይ ሴራ ሳይገነዘቡ በየጫካው ተበታትነው የሚገኙ ቀሪ የሽብር ቡድኑ አባላት ወደ ኅብረተሰቡ በመቀላቀል ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖሩ በአካባቢው አባ ገዳዎች ጥሪ ቀርቧል።