በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 41 ሚሊዮን መድረሱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በተገኙበት ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩ በነበረው የፓናል ውይይት ላይ የተሳተፉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በቴሌኮም ዘርፉ የተደረጉ ማስፋፊያዎችና ለውጦችን ዘርዝረዋል።
በዚህም በግልና በመንግስት የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች የሞባይል አገልግሎት ደንበኞች ቁጥር 85 ሚሊዮን መድረሱን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁለቱ የቴሌኮም የአገልግሎት አቅራቢዎች ከ96 ሚሊዮን በላይ ማስተናገድ የሚችል የኔትወርክ አቅም መፍጠራቸውንም ጠቅሰዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2018 በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 17 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 41 ሚሊዮን መድረሱን ተናግረዋል።
በመንግስትና በግል አጋርነት በተሰራ ማስፋፊያ 6 ነጥብ 3 ሜጋዋት (አይቲ ሎድ) የመሸከም አቅም ያለው የዳታ ማዕከል መገንባቱን ጠቅሰዋል።
ይህም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው ያነሱት፡፡
የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ የዲጂታል ክፍያን ማሳደግ የተገነባውን መሰረተ ልማት እሴት እንዲጨምር ማድረግ የተቻለበትን አሰራርም አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና እንዲሁም ዲጂታል ኢትዮጵያን በቀሪዎቹ አመታት እውን ለማድረግ የተጀመሩ የቅንጅት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም በመድረኩ መገለፁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡