በኦሮሚያ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች የህዝቡን ኑሮ እያሻሻሉ ነው፡- የክልሉ ኮሙኒኬሽን

31 Days Ago
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች የህዝቡን ኑሮ እያሻሻሉ ነው፡- የክልሉ ኮሙኒኬሽን

በኦሮሚያ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች የህዝቡን ኑሮ እያሻሻሉ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ገለጹ።

የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች የተከናወኑ የልማት ስራዎችን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በክልሉ ከለውጡ በፊት በግብርናና በኢንዱስትሪ ላይ ብቻ ታጥሮ የቆየውን የኢኮኖሚ መስክ በተለያየ መንገድ ማስፋት መቻሉን አመልክተዋል።

ከሁለቱ ዘርፎች በተጨማሪ ለቱሪዝም፣ ማዕድንና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መስክም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ሰፋፊ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን አስታውሰዋል።

በተለይም የግብርና ዘርፍ የክልሉ መንግስት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት፣ ለውጪ ገበያ የሚውሉ ምርቶችን በስፋት ማምረትና የስራ እድል ፈጠራ ምንጭ እንዲሆን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

በዚህም ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በተደረገ ጥረት በክልሉ አብዛኛው አካባቢዎች በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ ማረስ ተችሏል ነው ያሉት።

ከግብርና ዘርፍ የሚገኘውን ውጤት የበለጠ ለማሳደግ የክልሉ መንግስት ለግብዓት አቅርቦት እና ግብርናውን በቴክኖሎጂ ለማገዝ ሰፋፊ ስራዎች መስራቱንም ጠቅሰዋል።

በተሰራው ስራም የክልሉ አርሶ አደር ኑሮ ላይ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን አስታውሰው፤ በእነዚህ ዓመታት አገሪቷ ስንዴን ወደ ውጪ መላክ እንደትችል ክልሉ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ከመደበኛ የግብርና ስራ ጎን ለጎን በከተማ ግብርና፣ በማዕድን ልማትና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

በከተማ ግብርና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ የስራ እድል ለመፍጠርና ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አንጻርም ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል።

በተመሳሳይ በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በትምህርትና በጤና ዘርፍ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በህዝቡ ኑሮ ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማሳረፍ እንደተቻለ ተናግረዋል።

በተለይም ከትምህርት ጥራት ጋር እንደ አገር ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ  በክልሉ መንግስት ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ በህብረተሰብ ተሳትፎ ከ15 ሺህ በላይ 'ቡኡራ ቦሩ' የተሰኙ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል።

በትምህርት ቤት ምገባ ረገድም በክልሉ በተያዘው 2016 ዓ.ም 5 ነጥብ 3 ሚሊዬን ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አንስተዋል።

በተጨማሪም የ'ኢፋ ቦሩ' አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ የተከናወነ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ የተሻለ እውቀት መጨበጥ የሚችልባቸው በርካታ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል።

ትምህርት ቤቶቹ የተሻለ እውቀት ያላቸው ተማሪዎች በውድድር ተቀብለው ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች ባሻገር የውጪ አገር ቋንቋዎችን ጭምር እንዲማሩና ሁል ገብ እውቀት እንዲጨብጡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በጤና ዘርፍም ባለፉት ጥቂት ዓመታት 1 ሺህ 500 የጤና ተቋማት የተገነቡ ሲሆን፤ የሁለተኛ ትውልድ የጤና ኬላዎች ግንባታ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ችግረኞችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉንና የህብረተሰቡም የእርስ በርስ መረዳዳት ባህል እየተጠናከረ መምጣቱን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

 

 

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top