በኦሮሚያ ክልል ፊቼ ከተማ ፈረስን ለጭነት አገልግሎት የሚያውሉ ሰዎችን 60 ሺህ ብር ለመቅጣት የወጣው መመሪያ ተግባራዊ መደረግ ጀመሩን የፊቼ ከተማ ባህልና ቱሪዝም አስታውቋል።
ከመጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ እንዲደረግ የተወሰነው ይህ መመሪያ፤ በአባ ገዳዎች እና በሃደ ሲንቄዎች መደንገጉ ተጠቁሟል።
የመመሪያው መነሻ ፈረስ ከኦሮሞ ባህል እና ከማኅበረሰቡ ጋር ባለው ጥብቅ ቁርኝት ምክንያት መሆኑን የፊቼ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ኃላፊ ወ/ሮ ብርሃኔ ደርቤ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ገልፀዋል።
ፈረስ ለደስታ፣ለምስጋና እንዲሁም ለሀገራዊ ዘመቻ ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ድልን ያመጣ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ ይህን የሀገር ሀብት ባልተገባ መልኩ ልንይዘው አይገባም ብለዋል።
መመሪያው በፊቼ ከተማ ቀድሞ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰው፤ ሌሎች ወረዳዎች እና ቀበሌዎችም በተከታይነት እንደሚተገብሩት ጠቁመዋል።
"መመሪያውን ተገግባራዊ ከማድረጋችን በፊት፤ የጋሪ አገልግሎት በመስጠት ይተዳደሩ ለነበሩ ሰዎች የስራ መፈለጊያ በቂ ግዜ እና የስራ ዕድል አመቻችተናል" ብለዋል ኃላፊዋ።
በጋሪ አገልግሎት ስራ ላይ መቀጠል የሚፈልጉ ግለሰቦች ሌሎች አማራጮችን ሊጠቀሙ እንደሚገባ ነው ወ/ሮ ብርሃኔ የገለፁት።
ይህን ተላልፈው የሚገኙ አካላት በኦሮሚ ባህላዊ ፍርድ የ60 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጣልባቸውም ተናግረዋል።