በፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር የተመራ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በ148ኛው የዓለም ፓርላማዎች ኅብረት ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
148ኛው የኅብረቱ ጉባኤ "የፓርላማ ዲፕሎማሲ፡ ለሰላምና መግባባት ድልድይ መገንባት" በሚል መሪ ቃል በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከተማ እ.ኤ.አ ከመጋቢት 23 እስከ 27 ቀን 2024 ድረስ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
አቶ አገኘሁ ተሻገር በትናንትናው ዕለት በተካሄደው የጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ማድረጋቸው ተገልጿል።
አፈ ጉባኤው በሩሲያ ሞስኮ በሙዚቃ ኮንሰርት ተሳታፊዎች ላይ በደረሰው የሽብር ጥቃት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን በራሳቸውና በልዑካን ቡድኑ ስም ገልፀዋል።
በዓለም ላይ የሚታየውን የሰላምና ፀጥታ ችግር ለመቅረፍ የፓርላማ አባላት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት እንዲችሉ ጉባኤው በወሳኝ ወቅት መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ አቶ አገኘሁ በመድረኩ ተናግረዋል።
በጉባኤው የፓርላማ አባላት በቀጣይ ቀናት በሚኖራቸዉ ውይይት፤ በዓለም ላይ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚያስችሉ ሀሳቦች ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ጥሩ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
በተጨማሪም በአፍሪካ፣ በመካከለኛዉ ምስራቅ ፣ በዩክሬን እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚካሄዱ የተለያዩ ግጭቶችንና ጦርነቶችን ለማስቆም፤ ከፓለቲካዊ ቁርጠኝነት በተጨማሪ የፓርላማ አባላት ተሳትፎ በእጅጉ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በዓለሞ ላይ ሰላምና ፀጥታን ለማምጣት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗን ጠቅሰው፤ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተከሰቶ የነበረውን ግጭት መንግስት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ለመቋጨት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ቀጠናውን በኢኮኖሚ ማስተሳሰር ወሳኝ መሆኑን በማስታወስ፤ ኢትዮጵያ በቀጠናው ይህንን ለመፍጠር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ ወሳኝ ስራዎችን እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ሀገራዊ የምክክር መድረክ ማመቻቸትን ጨምሮ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተቱ በርካታ ውይይቶች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን አቶ አገኘሁ ተናግረዋል።
አፈ ጉባኤው በሩሲያ ፌደሬሽን በተዘጋጀው በብሪክስ አባል አገራት አፈ ጉባኤዎች መድረክ ላይ በመሳተፍ፤ የአባል አገራት የፓርላማ ህብረት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ኢትዮጵያ የበኩሏን ተሳትፎ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።
በአቶ አገኘሁ ተሻገር በተመራው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ውስጥ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጂጌ፣ እና ሌሎች የፌደሬሽን ምክር ቤትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች ፣እንዲሁም በጄኔቫ የኢዲፌዲሪ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ፀጋአብ ከበበውን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አባላት መካተታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።