21ኛው ዙር ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ ሩጫ ውድድር የፊታችን እሁድ ይካሄዳል

1 Mon Ago
21ኛው ዙር ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ ሩጫ ውድድር የፊታችን እሁድ ይካሄዳል

የ2016 ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች የ 5 ኪ.ሜ ሩጫ የፊታችን እሁድ መጋቢት 8 ቀን 16ሺ ተሳታፊዎች በሚገኙበት ይካሄዳል፡፡

የዘንድሮው የተሳታፊ ቁጥር በ20 አመት የውድድር ዘመን ውስጥ ትልቁ ሲሆን ከጤና ራጮች ባሻገር በ5 የተለያዩ ዘርፎች የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች መካተታቸው ተጠቅሷል፡፡

"የሴቶችን አቅም እንደግፍ፤ ለውጥን እናፋጥን" በሚል መልዕክት የሚደረገው የዘንድሮው ውድድር በአትሌቶች ዘርፍም ተጠባቂ የሚሆኑ አትሌቶችን በማሳተፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መታቀዱ ተጠቁሟል፡፡  

በውድድሩ ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ መልኩ የኢትዮ-አየርላንድ ግንኙነት 30 አመት   መሙላቱን አስመልክቶ 35 የሚጠጉ ከአየርላንድ የሚመጡ ተሳታፊዎች የሚካተቱ ሲሆን እነዚህ ተሳታፊዎች ከውድድሩ ተሳታፊነታቸውም ባሻገር በየአመቱ አየርላንዶች በደማቁ የሚያከብሩትና ባህላቸውን የሚያሳዩበት የሴንት ፖትሪክ አመታዊ በአል እንደሚያከበሩ ተመላክቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከሌላ የአለም ሃገራት የሚመጡ ከ40 በላይ ተሳታፊዎችም መካተታቸውን ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የማህበራዊ ትስስር ገፅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ይህን የቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ ውድድር በጋራ እያዘጋጁ እና የውድድሩ ቀን ተሳታፊዎችን ለማዝናናት እየሰሩ ያሉትን ሳፋሪኮም፣ የተባበሩት መንግስታት፣ ስንቅ ማልት፣ ዳሽን ባንክ፣ ሰንሲልክ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ችርስ ውሃ፤ ሃያት ሬጀንሲ እና ብቸኛው የሚዲያ አጋር የሆነውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) አመስግኗል፡፡

መጋቢት 8 ቀን የሚደረገውን ይህን ውድድር በቀጥታ ስርጭት በኢቢሲ መዝናኛ እና በፌስ ቡክ ገፅ እንዲሁም በኢቢሲ ቴሌግራም ቻናል እና በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ፌስ ቡክ ገፅ ከጠዋቱ 1፡30 ጀምሮ መከታተል ይቻላል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top