"ከቀን ወደ ቀን በትዳር ላይ እየተከሰቱ ያሉ ስብራቶች የትዳር ብቻ ሳይሆኑ የሀገር ስብራቶችም ናቸው" - የጋብቻ አማካሪው ሀበንዮ ሲሳይ

1 Mon Ago
"ከቀን ወደ ቀን በትዳር ላይ እየተከሰቱ ያሉ ስብራቶች የትዳር ብቻ ሳይሆኑ የሀገር ስብራቶችም ናቸው" - የጋብቻ አማካሪው ሀበንዮ ሲሳይ
ኢትዮጵያ ለትዳር ትልቅ ስፍራ ከሚሰጡ አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ይታወቃል፤ በሐይማኖትም ሆነ በባህል በኢትዮጵያ ትዳር ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው።
 
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፍቺ በተለይ በከተሞች አካባቢ እየጨመረ መምጣቱን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
 
ለአብነትም የካቲት 7/2016 ዓ.ም የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ያወጣውን መረጃ መጥቀስ ይቻላል።
 
ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መረጃው ላለፉት ስድስት ወራት ብቻ በአዲስ አበባ ፍቺ በ106.7 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ያመላክታል።
 
ኢቢሲ ሳይበር ይሄንን አስመለክቶ የጋብቻ አማካሪ የሆኑትን ሀበንዮም ሲሳይን አነጋግሯል።
 
እንደ አማካሪው ገለጻ ከሆነ ጋብቻ እና ትዳር የሚሉት ቃላት በተለዋዋጭነት የምንጠቀማቸው ቃላቶች ናቸው። ጋብቻ ከአንድ ሰው ጋር ብቻ የሚል ትርጉም እንዳለው ገልጸው፤ ትዳር የሚለው ቃል ደግሞ ሰፋ ያለ ትርጉም እንዳለው ያብራራሉ።
 
በማብራሪያቸውም፤ ትዳር የሚለው ቃል "ሀደረ" ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ እና ማስተዳደርን የሚያመለክት ነው ይላሉ፤ በዚህም ትዳር ማለት ትንሽ ሀገር መሆኑን ይገልጻሉ።
 
ትዳር ውስጥ በርካታ ነገሮች መኖራቸውን የሚያነሱት ባለሙያው፤ ከሐይማኖት አኳያ ደግሞ ትዳር ትልቅ ተቋም እና የሰው ዘር የሚቀጥልበት እንዲሁም የሚገነባበት መሰረት መሆኑን አብራርተው፤ በጥቅሉ ትዳር የህልውናችን መሰረት ነው ሲሉም ይገልጹታል።
 
ከቀን ወደ ቀን ግን በትዳር ላይ የሚከሰቱ ስብራቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ባለሙያ ገልጸው፤ እነዚህን ስብራቶች የትዳር ብቻ ሳይሆኑ የሀገር ስብራቶች ናቸው ይላሉ።
 
ትዳር አካላዊ እና መንፈሳዊ ምጣኔ ሀብታዊ ዝግጁነቶችን ይፈልጋል ያሉ ሲሆን ይሄ ሁሉ ዝግጁነት ሳይኖር ወደ ትዳር ዓለም መገባት እንደሌለበት ይናገራሉ።
 
ብዙዎች ስለ ትዳር ምንም ግንዛቤ እና ጤናማ አስተሳሰብ ሳይኖራቸው ወደ ትዳር መግባታቸው ለችግሩ አንዱ መንስኤ መሆኑን ባለሙያው ይጠቅሳሉ።
 
የጋብቻ ጽንሰ ሀሳቦች እየተጣሱ ናቸው ያሉት ባለሙያው፤ ትዳርን ለመመስረት ለትዳር የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን አሟልቻለሁ ወይ ብሎ ራስን መጠየቅ ሊቀድም ይገባል ብለዋል።
 
ለብዙዎች ትዳር መፍረስ የተለያዩ ምክንያቶችን ጠቅሰው፤ ትዳርን ችግር የሌለበት ዓለም አድርጎ ማሰብ፣ ትዳር ውስጥ ችግር ይገጥመናል ብሎ አለማሰብ እና የቤተሰብ ጣልቃ ገብነት በዋናነት የጠቀሷቸው ምክንያቶች ናቸው።
 
ለዚህም ሰዎች ወደ ትዳር ዓለም ከመግባታቸው በፊት ቅድመ ጋብቻ ስልጠና መውሰድ እና ችግሮችን ለመፍታት ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል ሲሉ ነው የገለጹት።
 
ግጭት በትዳር ውስጥ የማይቀር መሆኑን በመረዳት ሰዎች ወደ ትዳር ከመግባታቸው በፊት አዕምሮአቸውን ለዚህ ቢያዘጋጁ፤ በትዳር ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ሲሉ ምክረ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።
 
በተስሊም ሙሀመድ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top