ራስ ወሌ ብጡል (አባ ጠጣው)

10 Mons Ago 1663
ራስ ወሌ ብጡል (አባ ጠጣው)

ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የኅብር እና አንድነት ውጤት ነው፡፡ በዓድዋ ጦርነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ ተሳትፈውበት የድል ቀንዲል ያበሩበት መድረክ ነው፡፡

ራስ ወሌ ብጡል በቀደምትነት ከሚጠቀሱት የዓድዋ ጀግኖች አንዱ ናቸው፡፡ ራስ ወሌ ብጡል ከደብረ ታቦር ተነስተው ከየጁ፣ ከላስታ፣ ከራያ፣ ከዋድላ እና ደላንታ የተውጣጣ ከ10 ሺህ ጦር በላይ መርተው ነው ዓድዋ ላይ ያበሩት፡፡ በእሳቸው አመራር ሥር በልጃቸው በራስ ጉግሳ ወሌ እየተመሩ በጦርነቱ የተሳተፉ ሙስሊም የጦር አበጋዞች ሚናም ለድሉ በጣም የላቀ ነበር።

ቀኝ አዝማች ሀምዛ አበጋዝ፣ ቀኝ አዝማች መሐመድ በረንቶ፣ ባላምባራስ ይማም አምቡሎ፣ ፊታውራሪ ዓሊ ይማም፣ ሼኽ መሐመድ ሚዐዋ በዚህ በራስ ወሌ እዝ ሥር የተሰለፉ ሙስሊም የጦር አበጋዞች ነበሩ። አነዚህ የወሎ ሙስሊሞች የክርስቲያኖቹ የእነ ራስ ወሌ ብጡል የእነ እቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ የእነ ደጅ አዝማች አያሌው ብሩ የሩቅ ዘመዶች መሆናቸውን ተክለጻዲቅ መኩሪያ መዝግበዋል።  

ክርስቲያኑ አፄ ምንልክ በማርያም ገዝተው ተከተሉኝ ያሉትን የዘመቻ ጥሪ አዋጅ ተቀብለው የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው ለሀገራቸው እና ለራሳቸው ክብር ሲሉ ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር የተዋደቁት ሙስሊሞች ኅብረ-ብሔራዊነትን ያደመቁ እና ምንጊዜም የማይረሱ ናቸው።

ራስ ወሌ ብጡል (ወሌ አባ ጠጣው) የእቴጌ ጣይቱ ወንድም ናቸው፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በዳግማዊ ቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት በግዞት እያሉ ተዋውቀው ነበር። ምኒልክ ንጉሥ ተብለው ሥልጣን በጨበጡ ጊዜ ወደ ሸዋ መጥተው የደጅ አዝማችነት ማዕረግ አገኙ።

ታላቅ እህታቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር ከተጋቡ በኋላ ደጃዝማች ወሌ በላቀ አገልግሎታቸውም በአማችነታቸውም የራስነት ማዕረግ አገኙ።

ራስ ወሌ ከደብረ ታቦር ተነስተው ጦራቸውን እየመሩ ከሁሉም ቀድመው በአምባላጌ ግንባር የደረሱ ጀግና ናቸው። በዓድዋ ታላቅ ጀብድ እና አኩሪ ገድል አስመዝግበዋል። ከጦርነቱ በኋለም በጌምድርን እና የጁን አስተዳድረዋል። ራስ ወሌ በጀግንነታቸው ስመጥር ከመሆናቸው የተነሳ፡

ሰባት ደጃዝማች ዐሥር ፊታውራሪ የጠመቀውን፣

የወሌ ፈረስ ጠጣው ብቻውን፣

ወሌ በቡሎ ዘሎ ሲወጣ፣

ይመስላል ሐምሌ ክረምት የመጣ፣

ወሌ ወሌ ወሌ ቢሏችሁ፣

የሳቱ ጒማጅ መርጦ አለላችሁ።

የወሌ ፈረስ ቀጭኑ ቡሎ፣

ጅራቱ አውሳ ግንባሩ ወሎ።

ተብሎ ተገጥሞላቸዋል።

ራስ ወሌ ብጡል የንግሥት ዘውዲቱ ባል የነበሩትን ራስ ጉግሳ ወሌን፣ የራስ መንገሻ ዮሐንስ ባለቤት የነበሩትን ወይዘሮ ከፈይ ወሌን እና ደጅ አዝማች አመዴ ወሌን ወልደዋል።

"ተሸነፍን እንዳንል አሸንፈናል፣ አሸነፍን እንዳንል ጣልያን ሀገሩን እንደያዘ ነው፡፡ ኧረ የኋላ ኋላ ልጆቻችን ምን ይሉን ይሆን?" በማለት ከዓድዋ ድል ማግስት ጣሊያን ምጽዋን እና ኤርትራን ይዛ በመቆየቷ የተናገሩት እንደሆነ ታሪክ ያስታውሰናል፡፡

ራስ ወሌ ኅብር ጦራቸውን መርተው ጣሊያንን መቆሚያ መቀመጫ ሲያሰጡም እንዲህ ተብሎ ተገጥሞላቸዋል፡-  

ከጠመንጃው ይልቅ ያይኑ መመልከት፣

አባ ጠጣው ወሌ የእነ ጉግሳ አባት፣

ሰላቶ አባራሪ ዳገት ለዳገት።

ኅዳር 28 ቀን 1888 የፊታውራሪ ገበየሁን ጦር በተነኮሱት ጣሊያኖች ምክንያት በተደረገው የአምባላጌ ጦርነት ራስ ወሌ ብጡል ከልዑል ራስ መኮንን፣ ከፊታውራሪ ገበየሁ እና ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጋር በመሆን በቶሴሊ ከሚመራው የጣሊያን ጦር ጋር ገጠሙ፡፡ በዚህም ከ2 ሺህ በላይ ጣሊያን ወታደሮች ሲገደሉ ቶዜሊ ራሱ ተገደለ። የቶዜሊን ጦር ለማጠናከር በቦታው ደርሶ የነበረው ጄኔራል አሪሞንዲ በሕይወት የተረፉ 400 ሰዎችን ይዞ ወደ መቐለ ሸሽቶ አመለጠ።

ራስ ወሌ ብጡል (ወሌ አባ ጠጣው) በአድዋ ጦርነትም 10 ሺህ ጦራቸውን ይዘው በማይ ደላእታ ቦታቸውን ያዙ፡፡ በመጨረሻው ትንቅንቅም የድሉን ቀንዲል ካበሩ ምርጥ የጦር መሪዎች መካከል ሆነው ታሪካቸውን በወርቅ ቀለም ጽፈዋል፡፡

 

ለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top