የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘው ተሻገር ለወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገለጹ።
አፈጉባኤው ይህን ያሉት፤ የፌደሬሽን ምክር ቤት እና የፌደራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ በተፈራረሙበት ወቅት ነው።
የስምምነት ሰነዱ ሁለቱ ተቋማት የሀብት ማፈላለግ፣የአቅም ግንባታ እና የምርምር ስራዎችን በጋራ ለመስራት ያስችላቸዋል ተብሏል።
አፈጉባኤ አገኘው ተሻገር ሁለቱ ተቋማት የደረሱት ስምምነት፤ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን በዕውቀት እና በምርምር ለመመለስ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በስምምነቱ መሰረት የሚሰሩ ጥናቶች ሕገ መንግስቱን የመተርጎም እና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ስራዎችን በቀላሉ ለመፈፀም እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
የፌደራል ፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ፤ የፌደራል ስርዓቱን ለማጠናከር እና የዳበረ ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ በስምምነቱ መሰረቱ ተቋማቱ በጋራ ይሰራሉ ብለዋል።
የሁለቱ ተቋማት የጋራ ስምምነት የመንግስታት ግንኙነትን ማጠናከር፣በሕገ መንግስታዊነት እና በሕግ የበላይነት ላይ የአቅም ግንባታ በመስራት በክልል እና በፌደራል ደረጃ ተቀራራቢ የሕግ አተረጓጎም እንዲኖርም ያግዛል ተብሏል።