"ኮድ 4 የመኪና ሰሌዳ ያላቸው አሽከርካሪዎች አይቀጡም የሚል ሕግ የለም"- የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን

1 Mon Ago
"ኮድ 4 የመኪና ሰሌዳ ያላቸው አሽከርካሪዎች አይቀጡም የሚል ሕግ የለም"- የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን
የመኪና ሰሌዳ ኮዳቸው 4 የሆኑ አሽከርካሪዎች ሕግን ተላልፈው በሚገኙበት ወቅት በአብዛኛውን ጊዜ በትራፊክ ፖሊሶች ቅጣት ሲወሰድባቸው አይታይም፤ የሚል ሃሳብ በአንዳንዶች ዘንድ ሲነሳ ይስተዋላል።
 
ይህንን ሃሳብ በመያዝ ኢቢሲ ሳይበር የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ አማረ ታረቀኝ ጋር ቆይታ አድርጓል።
 
አቶ አማረ በምላሻቸው "ይህን በማህረሰቡ ውስጥ ያለ እሳቤ እኛም አስተውለነዋል፤ ሆኖም ግን የትኛውም አሽከርካሪ የትራፊክ ሕግጋትን በሚጥስበት ግዜ አስፈላጊ እርምጃ ይወሰዳል" ብለዋል።
 
ኮድ 4 ብቻ ሳይሆን ኮዳቸውን ወደ 2 እና 3 ቀይረው የሚያሽከረክሩ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር ሕግ ጥሰው ከተገኙ ከቅጣት እንደማያመልጡ አቶ አማረ ይናገራሉ።
 
ለአብነትም “ከአያት የሚመጡ ኮድ 4 መኪኖች አይቀጡም” የሚለውን የማህበረሰቡን ቅሬታ በመውሰድ ከ39 በላይ በሚሆኑ መኪናዎች ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል።
 
በሕግ ረገድ በተለየ ሁኔታ ለደህንነት፣ ለፖሊስ፣ ለእሳት አደጋ እና ለአንፑላንስ መኪናዎች ከሚሰጡት አገልግሎት አኳያ ጊዜ ሊሰጡ ስለማይችሉ ለአደጋ ተጋላጭ በማያደርጋቸው መልኩ ሕግጋትን ሊጥሱ እንደሚችሉ ገልጸው፤ ይህም በኢትዮጵያ ብቻ የሚደረግ ሳይሆን ዓለም አቀፍ አሰራር መሆኑን ያስረዳሉ።
 
"ኮድ 4 መኪና ስለሆነ ሕግጋትን መጣስ እችላለሁ" በሚል እሳቤ ለትራፊክ ፖሊስ የሚያስቸግሩ እና የሕጉን ተፈፃሚነት የሚያስተጓጉሉ አሽከርካሪዎች መኖራቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
 
አያይዘውም "እነዚህ አሽከርካሪዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ፤ የሰሌዳ ቁጥራቸው እንዲመዘገብ በማድረግ የተሽከርካሪውን መረጃ በመያዝ ከከንቲባ ፅሕፈት ቤት፣ ከፌደራል መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ከኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመሆን እየሰራን እንገኛለን" ሲሉ ገልፀዋል።
 
በደንብ 395/209 መሰረት ከላይ ከተጠቀሱት የስራ ዘርፎች ውጪ ያሉ ማንኛውም ኮድ 4 እንዲሁም የመንግስት ሆነው ኮድ 2 እና 3 የሆኑ መኪኖች ላይ እርምጃን እንደምንወስድ ሊታወቅ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
 
በማህበረሰቡ ዘንድ የተፈጠረውን እሳቤ ለማስቀረት በተለያዩ መድረኮች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሞክረናል ያሉት አቶ አማረ፤ ትልቁ ክፍተት የትራፊክ ፖሊሶች ሕግን የማስፈጸም ችግር መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል ብለዋል።
 
በአፎሚያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top