ከመስኖ ስንዴ ልማቱ የሚጠበቀውን ምርት ለማሳካት የሰብል እንክብካቤ ስራ እየተሰራ ነው

1 Mon Ago
ከመስኖ ስንዴ ልማቱ የሚጠበቀውን ምርት ለማሳካት የሰብል እንክብካቤ ስራ እየተሰራ ነው
በቅርብ ጊዜ በግብርናው በተለይም በስንዴ ልማት የመጣው ለውጥ ትልቅና በታሪክ የውጭ ገበያን የተሻገርንበት በመሆኑ በዚህ የተገኘው ተሞክሮ ይበልጥ እንዲስፋፋና በሌሎችም ሰብሎች እንዲደገም ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
 
የ10 ዓመቱን ሃገራዊ የልማት እቅድ ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ በተደረጉ ማሻሻያዎች ትልቅ ለውጥ የተገኘ ሲሆን በ2011 ዓ.ም በ3500 ሄክታር መሬት የተጀመረው የመስኖ ስንዴ በዘንድሮው ዓመት ከ3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 120 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
 
በ2016 ዓ.ም የበጋ መስኖ ስንዴ ፕሮግራም መነሻ አላማው ከውጭ የሚገባን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት ባለፈ የስራ እድል መፍጠርና በቂ ምርት ለኢንዱስትሪው ማቅረብ ሲሆን አሁን የወጪ ንግድና የአርሶአደሩን ገቢ ማሳደግን ተጨማሪ አላማ በማንገብ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡
 
በአሁኑ ሰዓት 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ በዘር የመሸፈን ስራው 98 በመቶ ደርሷል፡፡
 
የመስኖ ስንዴ ልማቱን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከመስኖ ስንዴ ዘር ሽፋን ጎን ለጎን የሰብል ጥበቃና እንቅብካቤ ስራው በስፋት እየተሰራ ይገኛል፡፡
 
በግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የተመራ ከፍተኛ የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮና የከተማ አስተዳደር አመራሮች በክልሉ ሸገር ከተማ አስተዳደርና ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ የመስኖ ስንዴ ልማቱ ያለበትን ደረጃ በመስክ በመገኘት ተመልክተዋል፡፡
 
ግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በያዝነው ምርት ዘመን የመስኖ ስንዴን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም በዘንድሮው የመስኖ ስንዴ ልማት በተለየ መልኩ 2.7 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው መሬት በጂፒኤስ የተያዘ ስለሆነ ለክትትልና ድጋፍ ስራ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
 
በመስክ ምልከታው ወቅት አርሶ አደሩና የግብርናው ባለሙያ በግብዓትና ውሃ አጠቃቀም ላይ ጥሩ አፈጻጸምን በማሳየታቸው የመስኖ ስንዴ ሰብል በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top