የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል 12.7 ቢሊዮን ብር በላይ የድጎማ በጀት ተመድቦ እየተሰራ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

10 Mons Ago 906
የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል 12.7 ቢሊዮን ብር በላይ የድጎማ በጀት ተመድቦ እየተሰራ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ከመንግስት ካዝና 12.78 ቢሊዮን ብር በላይ የድጎማ በጀት ተመድቦ እየተሰራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዓድዋ ድል መታሰቢያ የምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2016 የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀም ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ይገኛል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማብራሪያቸው፤ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ባለፉት 6 ወራት የምርት አቅርቦትን የማሻሻል፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የንግድ ስርዓቱን የማዘመንና የቁጥጥርና የክትትል ስራን የማጠናከር ስራ በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ከመንግስት ካዝና 12.78 ቢሊየን ብር በላይ የድጎማ በጀት መድቦ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

ይህ የድጎማ በጀት ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረው 8 ቢሊየን አንፃር ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ በማድረግ ከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ጫናን በመረዳት የሕዝብ ውግንናና ችግሩን ለማቃለል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ድጎማው በዋናነት በተማሪዎች ምገባ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት፣ በጤና መድሕን፣ በትራንስፖርት፣ በምርት አቅርቦትና ሌሎችም ተግባራት ላይ የዋለ መሆኑን መግለፃቸውን ከከንቲባ ፅ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በመንግስት ድጎማ የሚቀርቡ መሠረታዊ ፍጆታዎችን ለህብረተሰቡ በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ በተሰራው ስራ ከተመደበው ስኳር 168,000 ኩንታል ውስጥ 161,941 (96.3%) ኩንታል መሰራጨቱን እና በምግብ ዘይት በኩልም ከ 4,278,434 ሊትር ውስጥ 4,278,424 ሊትር የምግብ ዘይት ለማህበረሰቡ ማሰራጨት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የዳቦ አቅርቦትን ከማሳደግ አንፃርም በመንግስትና በግል ተቋማት አጋርነት በተሰሩ የዳቦ ፋብሪካዎች 67,107,133 ዳቦ የማሰራጨት ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡

የእሁድ ገበያ መዳረሻዎችን 179 በማድረስ በማዕከላቱ የምርት አቅርቦት መጠን፣ የምርት ጥራትና የተሳታፊዎችን ብዛት መነሻ ያደረገ ስታንዳርድ በማዘጋጀት የግብርና እና የኢንዱስትሪዎች ምርቶች በቀጥታ ለሸማቹ እንዲቀርብ በመደረጉ በገበያ ማረጋጋት ላይ አስተዋፅኦ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

አቅርቦት በማሻሻል የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በሌማት ትሩፋት የተጀመሩ የከተማ ግብርና ልማት ስራዎች በማጠናከር ምርታማነትን የማሳደግ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top