የካቲት 12 ሲታሰብ የማይረሳው ወጣት አርበኛ - ስምዖን አደፍርስ

7 Mons Ago 993
የካቲት 12 ሲታሰብ የማይረሳው ወጣት አርበኛ - ስምዖን አደፍርስ

የካቲት 12 ቀን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የማትረሳ ዕለት ነች፡፡ ቀኑ በአንድ በኩል ጣሊያን ያገኘው ድል ጊዜያዊ እንጂ እንደማያዘልቀው ኢትዮጵያውያን መልዕክት ያስተላለፉበት ዕለት ሲሆን፣ በክስተቱ ምክንያት ደግሞ የወረደው የጭካኔ በትር የፈሺስት ጣሊያንን ማንነት ያጋለጠ ነበር፡፡ ግራዚያኒ ላይ በተወረወረ ቦምብ ምክንያት ከ30 ሺህ ሰዎች በላይ የተጨፈጨፉበት የጭካኔ በትር ህዝቡ ውስጥ ፍርሃትን ከመፍጠር ይልቅ ህዝቡ ለወራሪው ያለውን የመረረ ጥላቻ ያባባሰም ነበር፡፡

ዕለቱን መራራ ያደረገችውን ግራዚያኒን የመግደል ሙከራ አቀነባብረው ከተገበሩት አርበኛ ወጣቶች መካከል አንዱ ስምዖን አደፍርስ ነበር፡፡

ለመሆኑ ወጣቱ አርበኛ ስምዖን አደፍርስ ማን ነው? ምንስ ጀብዱ ሠራ? የዛሬውን ዕለት የሰማዕታት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ የዚህን ጀግና ታሪክ በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

ስምዖን አደፍርስ የተወለደው በወቅቱ አጠራረር በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በሐብሮ አውራጃ አንጫር ወረዳ ልዩ ስሙ ጉባ ላፍቶ በተባለ ሥፍራ በ1905 ዓ.ም ነው። ትምህርቱን ጉባ ላፍቶ በሚገኘው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ደብር የጀመረ ሲሆን በልጅነቱ ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በልደታ ማርያም ካቴድራል እና በአሊያንስ ፍራንሴዝ ተምሮ አጠናቋል።

ትምህርቱን እንደጨረሰም ወንድሙ ከጅቡቲ ገዝቶ በላከለት ሁለት ኦፔል መኪናዎች የታክሲ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ በወቅቱ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ከነበሩት አናሳ ቁጥር ከነበራቸው ታክሲዎች መካከል የሱ ታክሲዎች ዘመናዊ አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል።

ወጣቱ ስምዖን ምንም እንኳን ጥሩ ገቢ እያገኘ የተሻለ ኑሮ እየኖረ የነበረ ቢሆንም፤ የሀገሩ በጣሊያን ወራሪ እጅ መውደቅ እና የወገኖቹ በዱር በገደል መንከራተት፣ የሕዝቡ መናቅ እና መዋረድ ያበሳጨውና እረፍት ይነሳው ነበር።

በዚህም ምክንያት በውስጥ አርበኝነት በመሳተፍ ወራሪውን ለመፋለም ወሰነ፡፡ ለአርበኞች መረጃ እና ስንቅ በማድረስም ሥራውን ጀመረ፡፡ ሁነኛ የውስጥ አርበኞችን ሲያፈላልግም ከአብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ጋር ተገናኘ፡፡

ሁለቱ ወጣቶች እንደ ስምዖን በግራዚያኒ የተበሳጩ እና እሱን ለመግደል መዘጋጀታቸውን ስምዖን ተረዳ፡፡ በሀሳብ ሲግባቡም ቀጣዩ እርምጃቸው ምን ሊሆን እንደሚችል በየቀኑ እየተገናኙ መወያየት ጀመሩ፡፡

ግራዚያኒን ለማስወገድም በጋራ በመሆን የግድያ ዕቅድ ያወጡ ጀመር፡፡ ከአዲስ አበባ በመውጣት ወደ ዝቋላ በመሄድ በግራዚያኒ ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃ እንደሚወሰድ እና እርምጃውን ከወሰዱ በኋላም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ዕቅድ ሲያወጡ ከረሙ፡፡ የቦንብ አፈታት እና አወራወርንም ሲለማመዱ ቆይተው ወደ አዲስ አበባ በመመለስ አመቺ ጊዜ መጠበቅ ጀመሩ፡፡

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሕዝብ ገነተ ልዑል (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ቤተ መንግሥት እንዲኝ ግራዚያኒ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ለድሆች ምጽዋት እንደሚሰጥ ስላስነገረም ብዙ ሰው ወደ ግቢው አመራ፡፡

ሦስቱ ወጣቶችም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ግራዚያኒን ለመግደል ተስማሙ፡፡ ለተልዕኮውም ሦስቱም ሥራ ተከፋፈሉ፡፡ አብርሃም እና ሞገስ የግራዚያኒ አስተርጓሚዎች ስለነበሩ ወደ ግቢ ገብተው ግራዚያኒን በቦምብ እንዲገድሉ፣ ስምዖን መኪናውን አዘጋጅቶ በአፍንጮ በር በኩል ጠብቋቸው ተልዕኮቸውን ሲፈጽሙ ይዟቸው እንዲሄድ ተስማሙ፡፡

ግራዚያኒ ሕዝቡን ሰብስቦ መደስኮር እና መደንፋት ጀመረ፡፡ የአርበኞችን ስም እየጠራ ማንኳሰስ፣ የጣሊያን መንግሥት ታላቅነት፣ ጣሊያንን የሚቃወሙ አርበኞች አንገት ቆርጦ ሮማ እንደሚልክ መዛቱን ቀጠለ፡፡

ግራዚያኒ በእብሪት ተወጥሮ ዲስኩሩን እያሰማ እያለ አብርሃም እና ሞገስ ቦምብ ጣሉበት፡፡ ግራዚያኒ እና ከእሱ ጋር የነበሩትን ጄኔራሎች ሲቆስሉ፣ የአውሮፕላን አብራሪ ጄኔራሉ ግን ሞተ፡፡

በተፈጠረው ረብሻ መካከልም ሦስቱ ወጣቶች በስምዖን ታክሲ በመሆን በአፍንጮ በር በኩል ወጥተው የጎጃምን መንገድ ይዘው በሱሉልታ በኩል ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄዱ፡፡ ስምዖንም እነሱን እዚያ አድርሶ ከሳምንት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የካቲት 19 ቀን 1929 ዓ.ም በባንዳዎች ተጠቁሞ ተያዘ፡፡

ከስምዖን ጋር የተያዘው ሠራተኛውን ለብቻው አስረው ምርመራ ያደርጉበት ጀመር፡፡ ስምዖን ጋር የሚመጡ ሰዎች ማን ማን እንደሆኑም ሠራተኛው በተናገረው መሰረት እያንዳንዳቸውን የስምዖን ጓደኞች ይዘው ገደሉአቸው፡፡

ስምዖንንም በመግረፍ፣ ፀጉሩን በመንጨት እና የጣቶቹን ጥፍር በመንቀል ሰቃዩን አበዙት፡፡ ይሁን እንጂ ስምዖን ከዓላማው ፍንክች ባለማለት ምስጢር አላወጣም አላቸው፡፡ ባንዳዎቹ እና ባዳዎቹም ከእርሱ ምንም ማግኘት አለመቻላቸውን ሲያውቁ ሚያዝያ 29 ቀን 1929 ዓ.ም. መርዝ ወግተው ገደሉት፡፡

ስምዖን ሲገደል የ24 ዓመት ወጣት ነበረ፡፡ ጣሊያኖች ሊያቃጥሉት የነበረውን አስከሬኑንም ቤተሰቦቹ በወርቅ በመግዛት በድብቅ ወስደው ግንቦት 1 ቀን 1929 ዓ.ም በጴጥሮስ ወጳውሎስ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብር አሳረፉት፡፡

ንብረቱንም ባንዳዎች እና ጣሊያኖቹ ተከፋፈሉት፡፡ ጣሊያኖቹ በባንክ የነበረውን ገንዘቡን ሲወስዱ፣ ባንዳዎቹ ደግሞ ታክሲዎቹን ወስደው ሲጠቀሙበት እንደኖሩ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሐምሌ 18 ቀን 1977 ዓ.ም እትሙ "ምን ሰርተው ታወቁ?" በሚለው አምዱ ሥር አስፍሯል፡፡

ኢትዮጵያ ተጠብቃ በነጻነት የኖረችው በእንደነ ስምዖን ዓይነቶቹ ወጣትነታቸውን ለሀገር ነጻነት መስዋዕት ባደረጉ፣ በመጦሪያ ዘመናቸው ዱር ቤቴ ብለው ለሀገር ዋጋ በከፈሉ እና ምንም ሳይጎድልባቸው ሁሉንም ትተው ለሀገራቸው ደማቸውን ባፈሰሱ አጥንታቸውን በከሰከሱ ጀግኖች ነው፡፡ 

ይሁን እና ሀገር ነጻነቷን ስታገኝ አፈ ጮሌዎቹ ባንዳዎች የድል አጥቢያ አርበኞች ሆነው ወደ ፊት በመምጣት ሥልጣኑን ተቆጣጠሩ፤ አብዛኛዎቹ አርበኞችም ተዘንግተው የትም ወደቁ፤ ታሪካቸውም አመድ የለበሰ መሰለ፡፡

የስምዖን ታሪክም እንዲሁ ሆኖ የሚገባውን ያክል ሳይዘከር ኖረ።  ይሁንና "እውነት እና ንጋት እያደር ይጠራል" እንዲሉ የነስምዖን አደፍርስ ዓይነት ለኢትዮጵያ ነጻነት ዋጋ የከፈሉ አርበኞች ታሪክ በእውነተኞቹ የሀገር ተቋሪቋሪዎች አቧራውን አራግፎ መነሳቱ አይቀርም፡፡

በለሚ ታደሰ

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top