በኦሮሚያ ክልል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት መስኮች አበረታች ስኬቶች ተመዝግበዋል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

10 Mons Ago 479
በኦሮሚያ ክልል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት መስኮች አበረታች ስኬቶች ተመዝግበዋል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት መስኮች አበረታች ስኬቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 3ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ለጨፌው ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤናና በስራ ዕድል ፈጠራ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በተለይም በግብርና ከ15ሺህ በላይ የሌማት ትሩፋት ማሳኪያ መንደሮች የተደራጁ ሲሆን፤ በዚህም ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ የወተት ላሞች በሰው ሰራሽ ስነ-ዘዴ ማዳቀል መቻሉን ገልጸዋል።

በዶሮ እርባታ ከ22 ሚሊዮን በላይ የአንድ ቀን ጫጩት የተሰራጨ ሲሆን፤ ከ19 ሚሊዮን በላይ እንቁላል መጣል የጀመሩ ቄብ ዶሮዎችን ባለፉት ስድስት ወራት ማከፋፈል መቻሉን አመልክተዋል።

በዚህም ያለፉት ስድስት ወራት የሌማት ትሩፋት ማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት መሰረት የተጣለበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።

በበጋ መስኖ ስንዴም ከሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የገለፁት አቶ ሽመልስ፤ የበጋ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የዝግጅት ስራዎች መካሄዳቸውንም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን የገለፁት አቶ ሽመልስ፤ ከአራት ሺህ በላይ የትምህርት ቤቶች ደረጃ መሻሻሉን አብራርተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ከሶስት ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በህዝብ ተሳትፎና በባለሀብቶች ተገንብተው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ ይህም የክልሉ መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየሰራቸው ላሉ ተግባራት ማሳያ ነው ብለዋል።

የመማሪያ መጻህፍት እጥረትን ለመፍታት የክልሉ መንግስት የማተሚያ ግብዓት አቅርቦት ችግሮችን ለማቃለል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በጤናው ዘርፍ የእናቶችና ህፃናት ጤና ለማሻሻል እንዲሁም በተቋማቱ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲረጋገጥ ስራዎች መሰራታቸውንም ተናግረዋል።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን ባነሱት ሀሳብ በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን መንግስት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለይም ባለፉት ስድስት ወራት የጨፌ አባላት ከህዝቡ የሚነሱ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማዳመጥ ምላሽ እንዲሰጥ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በዚህም ውጤት እየተገኘ ነው ሲሉም ተናግረዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top