በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የፈቃድ ማመልከቻዎችን መቀበል እጀምራለሁ:- የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን

2 Mons Ago
በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የፈቃድ ማመልከቻዎችን መቀበል እጀምራለሁ:- የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን
በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪነት የፈቃድ ማመልከቻዎችን መቀበል እንደሚጀምር የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
 
ባለስልጣኑ በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ አካላት ስራ ላይ በዋለው የፈቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር መመሪያ መሰረት መስፈርቶችን እንዲያሟሉም አሳስቧል፡፡
 
የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ቁጥጥር የሚደረግባቸውን የካፒታል ገበያ ተግባራት የሚያከናውኑ የንግድ ድርጅቶች መሆናቸውን መመሪያ ቁጥር 980/2016 ያትታል፡፡
 
በካፒታል ገበያ መሰማራት የሚቻልባቸው 15 የካፒታል ገበያ የአገልግሎት ዘርፎች የተለዩ ሲሆን፤ በዘርፎቹ ለመሰማራትም አግባብነት ካለው የመንግስት አካል የንግድ ምዝገባ የምስክር ወረቀት ማውጣት፣ በአክሲዮን ማህበር ቅርጽ የተቋቋመ ኩባንያ መመስረት፣ የተቀመጠውን ዝቅተኛ የካፒታል መመዘኛ ማሟላት፣ የድርጅቱን የዳይሬክተሮች ቦርድ እና ተሿሚ እንደራሴዎች መምረጥ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
 
በተጨማሪም የዳይሬክተሮችን ብቃት እና ተገቢነት ማረጋገጥ፣ የድርጅቱን የአሰራር ስርዓቶችን በሰነድ ማዘጋጀት እና ለባለስልጣኑ ማቅረብ፣ የመድን የዋስትና ሽፋን መግባት እንዲሁም የማይመለስ የማመልከቻ እና የፈቃድ ክፍያ መክፈል መሆናቸውን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top