ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት፣ በሮም ጣልያን በተሰናዳ ክብረ በዓል የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ተሸልመዋል።
ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ አመራር እና ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆነው ከባቢያዊ ሁኔታ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ ዕውቅና ለመስጠት የተበረከተ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ ልዑካን ቡድኖች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ በጣልያን የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ተልዕኮዎች አባላት እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተወካዮች በተገኙበት ሽልማቱን መቀበላቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ላለፉት አምስት ዓመታት በግብርናው መስክ ቁልፍ ኢንቨስትመንቶችን ያደረገች ሲሆን በስንዴ ምርት ራስን የመቻል ሥራዎችን በማከናወን በዐበይት ምርቶችም ላይ ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግባለች።