ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስጠሩ በርካታ አትሌቶች ከትግራይ ክልል የተገኙ ናቸው -ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ

11 Mons Ago 562
ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስጠሩ በርካታ አትሌቶች ከትግራይ ክልል የተገኙ ናቸው -ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ

ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስጠሩ በርካታ አትሌቶች ከትግራይ ክልል የተገኙ በመሆናቸው በቀጣይ ተተኪዎችን ለማፍራት ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በቅርበት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ገለፀች።

የ2024 ፓሪስ ኦሎምፒክ ሀገር አቀፍ የችቦ ቅብብሎሽ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል።

በችቦ ቅብብሎሽ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ እና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።

መርሃ-ግብሩ በመጪው ሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ለሚካሄደው 33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ በማህበረሰቡ ዘንድ ከወዲሁ መነቃቃት መፍጠርን ዓላማ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል።

አትሌት ደራርቱ በወቅቱ እንደተናገረችው የኦሎምፒክ የችቦ ቅብብሎሽ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ በመቀሌ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።

የኦሎምፒክ ችቦው ወደ ሁሉም ክልሎች ጉዞ ካደረገ በኋላ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ፍፃሜውን እንደሚያገኝ ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ተናግራለች።

ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስጠሩ በርካታ አትሌቶች ከትግራይ ክልል ወጥተዋል ያለችው ረዳት ኮሚሽነሯ፤ በቀጣይም ተተኪዎችን ለማፍራት ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ገልጻለች።

ኦሎምፒክ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ የኦሎምፒክ ችቦው በመላው ሀገሪቱ ሲዘዋወር የኢትዮጵያን አንድነት የምናጠናክርበት መሆን አለበት ስትልም ተናግራለች።

ቀጣይ ተረኛ የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ችቦውን ተረክቧል።

የኦሎምፒክ ችቦውን የተረከቡት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰይድ አልበሽር በበኩላቸው፤ የችቦ ቅብብሉን በድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የክልል አመራር አባላት በመገኘት የኦሎምፒክ ችቦውን በመያዝ የእግር ጉዞ ተደርጓል፤ የተለያዩ ስፖርታዊ ክንውኖችም ተስተናግደዋል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top