በጉጉት የሚጠበቁት የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ነገ ይጀምራሉ

10 Mons Ago 747
በጉጉት የሚጠበቁት የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ነገ ይጀምራሉ

ብዙ ያልተጠበቁ ክስተቶች የታዩበት 34ኛዉ የአፍሪካ ዋንጫ ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች በነገው ዕለት መካሄድ ይጀምራል።

ባኮትዲቯር አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ዋንጫ 24 አገራት በ6 ምድብ ተከፍለዉ 36 የምድብ ጨዋታዎችን ያደረጉ ሲሆን በአጠቃላይ 90 ግቦች ተቆጥረዋል።

ብዙ ያልተጠበቁ ክስተቶች የታዩበት የዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ለአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸዉ አገራት ከምድባቸዉ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በእግር ኳስ አፍቃሪያን ለዋንጫዉ ግምት ተሰጥቷቸዉ የነበሩት እንደ ጋና፣ ቱኒዚያ እና አልጄሪያ ያሉ ሀገራት ከምድባቸዉ ማለፍ እንኳን ተስኗቸዋል።

የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም የምድብ ጨዋታዎችን አሸንፎ ወደ ጥሎ ማለፍ መቀለቃሉ አዲስ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል።

የምስራቅ አፍሪካ ብቸኛ ተወካይ ታንዛንያን ጨምሮ የጋና፣ የአልጄሪያና የጋምቢያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች መሰናበታቸዉ የዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ሌላኛው ክስተት ነው።

ደጋፊዎቿ አንገታቸዉን የደፉባት አዘጋጇ አገር ኮትዲቯር በጭንቅ  ወደ ጥሎ ማለፉ መቀላቀሏ የአፍሪካ ዋንጫው ሌላዉ ገፅታ ነበር።

ጥሎ ማለፉን የተቀላቀሉ ሀገራት ከነገ ጀምሮ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን በዚህም ነገ ምሽት 2 ሰዓት አንጎላ ከ ናሚቢያ እንዲሁም ምሽት 5 ሰዓት ናይጄሪያ ከ ካሜሮን ይጫወታሉ።

የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎቹን ኢቢሲ በኢቲቪ መዝናኛና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮቹ እንዲሁም በአንጋፋው የኢትዮጵያ ሬዲዮና በኤፍኤም አዲስ 97.1 በቀጥታ ወደ አድማጭ ተመልካቾች ያደርሳል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top