የሸዋል ኢድ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ በቱሪዝም ዘርፍ የምናደርገው እንቅስቃሴ እንዲጠናከር ያደርገዋል - አቶ አደም ፋራህ

7 Mons Ago
የሸዋል ኢድ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ በቱሪዝም ዘርፍ የምናደርገው እንቅስቃሴ እንዲጠናከር ያደርገዋል - አቶ አደም ፋራህ

የሸዋል ኢድ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ መመዝገቡ በቱሪዝም ዘርፍ የምናደርገው እንቅስቃሴ እንዲጠናከርና አድማሱን እንዲያሰፋ ያደርገዋል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለፁ።

ኃላፊው የሸዋል ኢድ በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ምክንያት በማድረግ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ሀረር ከተማን በዩኔስኮ ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ የሀገራችን ከተማ የሚያደርጋት ሲሆን፤ ሀገራችን ኢትዮጵያንም በርካታ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራን እንድትይዝ የሚያደርጋት በመሆኑ ደስታችን ወደር የለውም ብለዋል አቶ አደም።

በቀጣይም የበዓሉ አከባበር ይበልጥ ባማረ መልኩ እንዲቀጥል እና ድምቀቱ ዓለም አቀፍ እውቅናውን በሚመጥን መልኩ እንዲካሄድ፣ ከተማዋም በቱሪስቶች ዘንድ ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን እንደ ብልፅግና ፓርቲ ሰፊ ስራዎችን መስራታችንን እንደምንቀጥል በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ መስህቦች ይበልጥ እንዲያድጉና ለሀገሪቱ የብልፅግና ጉዞ ተጨማሪ አቅም መፍጠር እንዲችሉ ፓርቲው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንም ኃላፊው በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top