የዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ሕብረት 386ኛ ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

8 Mons Ago
የዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ሕብረት 386ኛ ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

ሲምፖዚየሙ የሚካሄደው "ጥቁር ሰማይና የስነ-ፈለክ ቅርሶች አስትሮ ቱሪዝምን ለማሳደግ ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

በሲምፖዚየሙ ላይ አፍሪካ፣ እስያና አውሮፓን ጨምሮ ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት የመጡ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ናቸው።

ሲምፖዚየሙ የተዘጋጀው በዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ሕብረት (IAU)፣ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ቱሪዝም ሚኒስቴር የጋራ ትብብር ነው።

የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የቀጣናዊ ትስስር መሪ ስራ አስፈጻሚና የሲምፖዚየሙ ሰብሳቢ አቶ አለምዬ ማሞ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ሲምፖዝየሙ በምሽት የሚታይ የተፈጥሮ የሰማይ ብርሃንን ከሰው ሰራሽ ብርሃን የመጠበቅና የስነ-ፈለክ ቅርሶችን የተመለከቱ ምርምሮች የሚቀርቡበትና የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ነው።

የስነ-ፈለክ ቱሪዝምን ማሳደግና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን እምቅ የጨለማ ሰማይ የቱሪዝም ሀብት ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

ከቱሪዝም ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር በዘርፉ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግና የቱሪዝም ሀብቱን መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።

ሲምፖዚየሙ እስከ ሕዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ሕብረት ሲምፖዚየምን ስታዘጋጅ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2019 356ኛውን የሕብረቱን ሲምፖዚየም ማስተናገዷ የሚታወስ ነው።

እ.አ.አ በ1919 የተቋቋመው ዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ሕብረት ኢትዮጵያን ጨምሮ 85 አባል አገራት አሉት።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top