ለድርቅ ተጎጂዎች የዘላቂ መፍትሔ ፍኖተ ካርታ እንደሚዘጋጅ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ

1 Yr Ago
ለድርቅ ተጎጂዎች  የዘላቂ መፍትሔ ፍኖተ ካርታ  እንደሚዘጋጅ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ
ለድርቅ ተጎጂዎች እየተደረገ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ከማጠናከር ጎን ለጎን የዘላቂ መፍትሔ ፍኖተ ካርታ እንደሚዘጋጅ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የድርቅ አደጋዎች ምላሽ የአራት ወራት እቅድና አፈጻጸም ላይ ተወያይቷል።
በውይይቱ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሚኒስትሮችና የሴክተር መሥሪያ ቤት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ በድርቅ ተጎጂ ለሆነው ማኅበረሰብ አስቸኳይ ምላሽ መስጠት እየተደረገ ያለው ርብርብ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ምክር ቤቱ ባለፈው አንድ ወር ያከናወነው የድርቅ አደጋ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ መልካም መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት በድርቅ ተጎጂ በነበሩ አካባቢዎች እየዘነበ ያለውን ዝናብ በአግባቡ ለመጠቀምና የጎርፍ አደጋ ጉዳት እንዳያደርስ መረባረብ እንደሚገባም አንስተዋል።
በጤና፣ የውሃ፣ የግብርና የመስኖና ቆላማ ተቋማት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በተለይም የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦትና የመኖ ዝግጅት ትኩረት ሊሠጣቸው ይገባል ነው ያሉት።
በቀጣይም መረጃ ላይ የተመሠረተ የተረጂዎችን ቁጥር በመለየት ምላሽ የመሥጠት ሥራን በቅንጅት ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ድርቅና ግጭት ያስከተሉትን ችግር ለመሻገር የሚያስችል አገራዊ አቅም መኖሩን ገልጸው ሰብዓዊ ድጋፎችም ለተረጂዎች በቀጥታ መድረሳቸውን ማረጋገጥ የሁሉም የቤት ሥራ ነው ብለዋል።
መጪውን ጊዜ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመሻገር ድርቅ ጎርፍና ግጭት ያመጧቸውን ፈተናዎች በመቋቋም ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም አለብን ነው ያሉት።
ለዚህም ከፌደራል እስከ ክልል ሁሉም ተቋማትና አጋር አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን እንዲያጠናክሩ አሳስበው ምክር ቤቱም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በቀጣይም ለሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ዘላቂ መፍትሔ ሊቀመጥ እንደሚገባ ገልጸው በተለይም የቆላማ አካባቢ ልማት በመካከለኛ ዘመን እቅድ ውስጥ በአግባቡ መካተቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለአስቸኳይ ጊዜ የአደጋ ምላሽ መረባረብና የዘላቂ ጊዜ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀትም የቀጣይ ሥራችን ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሺፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው፣ ከመጋቢት ጀምሮ እየተተገበረ ባለው የድርቅ አደጋ ምላሽ እቅድ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የድርቅ ተጎጂ የሆኑ ከ11 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መኖራቸውን አንስተው የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ለሚሹ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ፈጣን ምላሽ መስጠትን ጨምሮ በየደረጃው አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ስለመሆኑም እንዲሁ።
በተለይም ድርቁና ሰሞኑን እየጣለ በሚገኘው ዝናብ በፈጠረው ጎርፍ ምክንያት የሰው ህይወት እንዳይጎዳ በተቋማዊ ቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
የሴክተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎችም በጤና፣ በግብርና፣ በመስኖ፣ በውሃ ዙሪያ በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል።
የበሽታ ሥጋት ክትትል፣ ህክምና፣ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮና ዘላቂ የቆላማ አካባቢ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተነስቷል።
የእንስሳት በሽታ እንዳይከሰት መከላከልና በቂ መኖ አቅርቦት ላይም እንዲሁ።
በድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠትም በመካከለኛ ዘመን እቅድ አካትቶ እንዲሠራ አቅጣጫ ተቀምጧል።
የፌደራልና የክልል አስቸኳይ ጊዜ የአደጋ ምላሽ ማስተባበሪያዎች በተቀናጀ መልኩ እየሠሩ ሲሆን የጎርፍ አደጋ መከላከል ግብረ ኃይል መቋቋሙ ተገልጿል።

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top