የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ባንኮች ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ ገለፀ

1 Yr Ago 544
የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ባንኮች ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ብሔራዊ ባንክ ገለፀ
የውጭ ባንኮች በሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲሳተፉ መፈቀዱን ተከትሎ ለዚሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለፀ።
የባንኩ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዝን ምክትል ገዢ አቶ ሰለሞን ደስታ፥ በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ ዝግጅት እየተከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል ።
ከዚህ ቀደም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀው ፖሊሲ ላይ የአዋጅ ረቂቅ ዝግጅትም ተጠናቋል ብለዋል።
በጉዳዮ ዙሪያ ሃሳባቸውን ያካፈሉን የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር አረጋ ሹመቴ፥ የውጭ ተቋማት በሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲሳተፉ ማድረግ ቴክኖሎጂን በማሳደግ እንዲሁም የስራ እድልን እና የካፒታል አቅምን በመፍጠር ረገድ ሚናው ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
እርምጃው ሀገሪቱ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ ሁኔታ የምታሳይበት እጋጣሚን የሚፈጥር እንደሆነም የምጣኔ ሃብት ተመራማሪው ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ ጤናማ የገበያ ውድድር እንዲፈጠር በቂ ዝግጅት መደረግ አለበት ብለዋል።
የብሄራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዝን ምክትል ገዢው አቶ ሰለሞን ደስታ በበኩላቸው፥ ወደ መጨረሻ ምዕራፍ ላይ የደረሰው የአዋጁ ረቂቅ የዘርፉን ተገማች ተፅዕኖዎች ከግምት ያስገባ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ እና መሰል ዝግጅቶች ይደረጉ ዘንድ ለባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፤ ዓለም አቀፍ የባንክ ስራዎችን ከሚቆጠጠሩ ተቋማት ጋር በጋራ የሚከናወኑ ስራዎችም እንዳሉ ጠቁመዋል።
በአወል አበራ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top