ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምዕራብ ጉጂ ገላን ወረዳ በቀርጫንሼ ትሬዲንግ የለማውን የቡና እርሻ ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቦታው ላይ ያየሁትና የተማርኩት ነገር አንድ ሰው እንዴት ሀገር እንደሚሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የኮፊ አረቢካ ቡና መገኛ መሆኗን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚነስትሩ፤ አሁን ባለው የቡና ምርት መጠን በሄክታር የሚገኘውና ትልቅ የሚባለው 10 ኩንታል መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀርጫንሼ ትሬዲንግ የለማው የቡና እርሻ በሄክታር 60 ኩንታል የሚገኝበት ነው፣ ይህ ደግሞ እጅግ አስደናቂ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ንፁህ ውኃ የሚያገኘው እና በማሽን የሚለቀምው ይህ እርሻ ብክነትን አያስተናግድም።
ይህ ተሞክሮ ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቢሸጋገር፣ በሄክታር 20 ኩንታል እንኳን ቢገኝ የምርት መጠኑን በእጥፍ ማሳደግ ይቻላልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በታሪኳ በዚህ ዓመት በቡና ኤክስፖርት ትልቅ የሚባለውን ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል።
በተደጋጋሚ የቡናው ዘርፍ እያደገ ነው፤ኢትዮጵያም በቡናው ዘርፍ እምርታ እየጨመረች ነው፤ የቡና ኤክስፖርቱም ያድጋል ሲባል የነበረው ከመረጃ ውጭ ሆኖ አልነበረም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ባለፉት ዓመታት በቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞች ተተክለዋል፣ ከዚህ ባለፈ በቀርጫንሼ ትሬዲንግ የለማውን የቡና እርሻ መመልከት በቂ ነው ሲሉ ነው የገለጹት።
በቀርጫንሼ ትሬዲንግ የቡና እርሻ ማሳ 750 ሄክታር መሬት ቡና ተዘርቶበት እየተለቀመ የሚገኝ ሲሆን ከ45 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።
1 ሺህ ሄክታር ባልሞላ መሬት ውስጥ ይህንን ያህል ምርት ከተገኘ. ባለን አቅም ብናመርት ምን ያህል የምርት መጠናችንን መቀየር እንደምንችል ማሳያም ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የመስርያም፣ የመንቂያም ጊዜአችን አሁን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ የቡና እርሻ ቦታ ከ5 ዓመታት በፊት ብንመጣ ምንም አናገኝም ነበር፤ ነገር ግን ቦታውን ቀይሮ በጥቂት ዓመት 45ሺ ኩንታል ቡና ማግኘት ቀላል አይደለም ሲሉ ገልፀው፤ ይህ ውጤት በተመቻቸ ሁኔታ እንዳልተገኘ ልብ ሊባል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ጉጂ ለግብርና ምቹ የሆነ አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደዚህ ያሉ የሀገር ሐብቶችን በመንከባከብ ፣የአካባቢን ሰላም በማስጠበቅ ጉጂን ፣ኦሮሚያን ብሎም ኢትዮጵያን ማልማት ቻላል ነው ያሉት።
አሁን ኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመኗን ጀምራለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ለዚህም በቡና ምርት እየተገኘ ያለው ውጤት ማሳያ ስለመሆኑ ተናግረዋል።