የአባ ገዳዎች ድርሻ ማስታረቅ እና ችግር የደረሰባቸውን መርዳት እንደመሆኑ ይህን ነው ያደረግነው - አባ ገዳ ተሬሳ ኢዴቲ

16 Days Ago 155
የአባ ገዳዎች ድርሻ ማስታረቅ እና ችግር የደረሰባቸውን መርዳት እንደመሆኑ ይህን ነው ያደረግነው - አባ ገዳ ተሬሳ ኢዴቲ

በመጫ ገዳ የኦዳ ብስል አባ ገዳዎች ሕብረት አባል የሆኑት አባ ገዳ ተሬሳ ኢዴቲ በመንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል በተደረገው የሰላም ስምምነት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ አካላት ወደ ሰላም ስምምነቱ እንዲመጡ አባ ገዳዎች ትልቅ ሚና መጫወታቸውን የጠቀሱት አባ ገዳ ተሬሳ፣ ወደ ሰላም የተመለሱት እንዳሉ ሆነው ቀሪዎቹም ወደ ሰላም እንዲመለሱ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የአባ ገዳዎች ድርሻ ማስታረቅ እና ችግር የደረሰባቸውን መርዳት ስለሆነ በዚሁ ሁኔታ ነው አሁን ወደ ሰላም የመጡትንም ያስታረቅነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

እናቶች እና አባቶች፣ አባ ገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላም እንዲመጣ ሲማጸኑ እንደ ነበረ እና ሕዝቡም ፈረሱን ለጉሞ ከለቻ እና ጫጩ አውጥቶ ልጆቹን ቀንበር ጠምዶ ስለ ሰላም መማጸኑን አስታውሰዋል፡፡

ሰላም እንዲጠፋ የሚሠሩት ሕዝብ ውስጥ ተመሳስለው ያሉት ናቸው ያሉት አባ ገዳ ተሬሳ፤ አሁን የተደረሰበት የሰላም ስምምነት እንዲደረግ አባ ገዳዎች ትልቅ ድርሻ መወጣታቸውንና በሁለቱም ወገን ስምምነቱን የሚጥሱ እንዳይኖሩ አባ ገዳዎች ዋስትና ሰጥተናል ብለዋል፡፡

በተለይም ታጣቂዎቹ ወደ ስምምነቱ ለመምጣት ጥርጣሬ እንዳይፈጠርባቸው አባ ገዳዎች ቃል እንደገቡላቸውና ያለውን አፈጻጸምም እንደሚከታተሉ ተናግረዋል፡፡

ይህን ስምምነት የሚጥስ ቢኖር አባ ገዳዎች የቅጣት አዋጅ እንሚያወጁም ነው አባ ገዳ ተሬሳ የተናገሩት፡፡

የሰላም ስምምነቱን የሚተቹት የተሳሳተ መንገድ ላይ እንደሆኑ ጠቅሰው፣ አሁን ያለው የሕዝቡ ስቃይ እንዲያበቃ ሰላም ዋነኛው መፍትሄ ስለሆነ እነዚህ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡

ሰላምን መርጠው የተመለሱ ታጣቂዎች እና አመራሮችም ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ እንደማይሟላ ተረድተው ወደ ፈለጉት አቅጣጫ እስኪሰማሩ ድረስ ጉድለቶች እንኳን ቢኖሩ መታገስ አለባቸው ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ሰላም በማጣት ለብዙ ስቃይ መዳረጉን ያወሱት አባ ገዳው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ሆኖ ለኦሮሞ ሕዝብ መገዳደል መፍትሔ እንደማያመጣ ከመጣንበት መንገድ መረዳት አለብን ብለዋል፡፡

በውጭ ሀገር እና ጦርነት በሌለባቸው ቦታዎች ሆነው የሕዝቡን የሰላም ጥያቄ የሚያጣጥሉ ወገኖችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አባ ገዳ ተሬሳ አሳስበዋል፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top