የክልሉ ሕዝብ አንድነቱንና የጋራ እሴቶቹን አጠናክሮ የልማት ሥራውን በተሻለ መልኩ እያከናወነ ነው፡- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

93 Days Ago 282
የክልሉ ሕዝብ አንድነቱንና የጋራ እሴቶቹን አጠናክሮ የልማት ሥራውን በተሻለ መልኩ እያከናወነ ነው፡- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባዔ ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ አባላት በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ተወያይተዋል።
 
ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፣ ክልሉን የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት ለማድረግ በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት እየተመዘገበ ነው።
 
በተለይ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ገልጸዋል።
 
"ሰላማችንን በሰላሙ ጊዜ እንሥራ" በሚል መሪ ሀሳብ የፀጥታ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን በማሳተፍ አብሮነትንና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ሲሰራ መቆየቱን አመልክተዋል።
 
በክልሉ የሰላምና ፀጥታ ሥራዎችን ለማጠናከር ክልላዊ የፀጥታ ምክር ቤትና የሃይማኖት ተቋማት ፎረሞች በየደረጃው መቋቋማቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
 
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አለመግባባቶችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ መፍታት በሚቻልበት አግባብ ላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉብት ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
 
ከክልሉ ምስረታ ጀምሮ የከተሞች ፎረም፣ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የዘመን መለወጫ በዓላት በሰላም መከበራቸውን አስታውሰው፤ በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ሲስተዋሉ የነበሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ተችሏል ብለዋል።
 
የክልሉ ሕዝብ አንድነቱንና የጋራ እሴቶቹን አጠናክሮ የልማት ሥራውን በተሻለ እያከናወነ መሆኑንም አቶ ጥላሁን ገልጸዋል።
 
በክልሉ ብዝሃነት፣ አብሮነት፣ መቻቻል እና የሴኩላሪዝም አስተሳሰብን ማጎልበት የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
 
በዚህም ክልሉን የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት ለማድረግ ያስቀመጥነው ራዕይ ውጤት አስመዝግቧል ነው ያሉት።
በቀጣይም ክልሉን የአስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ባለቤት ለማድረግ ሕዝቡንና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
ምክር ቤቱ የክልሉ አስፈጻሚ አካላትን የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top