የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ያሰለጠናቸውን ከ2 ሺህ በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራንን አስመረቀ

3 Mons Ago 281
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ያሰለጠናቸውን ከ2 ሺህ በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራንን አስመረቀ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በደብረ ብርሀን እና አሰላ የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት በአማርኛና አፋን ኦሮሞ ስርዓተ ትምህርት በዲፕሎማ መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 27 የቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራንን በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አስመርቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምርቃቱን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ መርሀ-ግብሩ አዲስ አበባን ህጻናትን ለማሳደግ ምርጥ አፍሪካዊት ከተማ ለማድረግ የጀመርነውን ራዕይ ለማሳካት ያለመ ነው ብለዋል፡፡  

ዛሬ የተመረቁትን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ዙሮች 3 ሺህ 685 መምህራንን ተመርቀው ወደ ስራ መግባታቸውንም ገልጸዋል።

ህጻንነት የሰው ልጅ በዕውቀት፣ በስነ ምግባር፣ በአካልና በአእምሮ እንዲሁም በሁለንተናዊ እድገት የሚገነባበት እድሜ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ የከተማ አስተዳደሩ በዚህ እድሜ ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህ ጨቅላ እድሜ ተገቢውን ኢንቨስትመንት ካደረግን እና መልካም ዘርን ከዘራን ነገ ጣፋጭ እና መልካም ፍሬን በማፍራት ይከፍለናል ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክለውም፤ ያልዘራነውን እንደማናጭድ ገብቶን ሁላችንም ይህንን ፕሮግራም በመደገፍ እንድናሳካው ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top