ለሊዝ ፋይናንስ ተጠቃሚዎች ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ተላልፉል - የኢትዮጵያ ልማት ባንክ

2 Mons Ago
ለሊዝ ፋይናንስ ተጠቃሚዎች ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ተላልፉል - የኢትዮጵያ ልማት ባንክ

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ለሊዝ ፋይናንስ ተጠቃሚዎች ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ መተላለፉን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በማእድን ዘርፍ ለተሰማሩ 14 ኤክስካቫተር፣ በቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ 28 የቱር ኦፐሬተር መኪኖች እና ለኮንስትራክሽን ስራ የሚሆኑ 7 ሎደሮች ለደንበኞቹ በሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)፤ በርክክቡ ላይ ባደረጉት ንግግር የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ከፍተኛ እድገት እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

በቱሪዝም፣ በኮንስትራክሽን እንዲሁም በማዕድን ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ዜጎች የሚያደርገው ድጋፍ በየጊዜው እያደገ መሆኑንም አንስተዋል።

ከአራት አመታት በፊት ይሰጥ የነበረው 4 ነጥብ 3 ቢልዮን ብር እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ በስድስት ወራት 10 ቢሊዮን ብር መሰጠቱን ተናግረዋል።

የሊዝ ፋይናንሲንግ በብድር አመላለሱም በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተላለፉት ማሽነሪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የተበላሸ ብድር መጠን 36 በመቶ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ወደ 1 ነጥብ 6 በመቶ መውረዱን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ባንኩ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በሚያደርጋቸው ውይይቶች እንዲሁም የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ተጠቃሚዎች እንዲረዱት በማድረግ የተገኘ ውጤት መሆኑንም አብራርተዋል።

ተጠቃሚዎችም የተረከቧቸው ማሽነሪዎች እያከናወኑ ያሉትን ስራዎች በተጠናከረ አቅም ለመስራት የሚያግዛቸው መሆኑን ገልጸዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top