ጉቦ ማቀባበል የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት

10 Mons Ago 1167
ጉቦ ማቀባበል የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት

ጉቦ ማቀበል

ከሙስና አይነቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ጉቦ ወይም መደለያ የመስጠትና የመቀበል የወንጀል ተግባር ውስጥ፤ ሰጪና ተቀባይ ብቻ ሳይሆኑ አንዳንዴ ጉቦ አቀባባዮችም ይሳተፉበታል፡፡ በዛሬው ፅሁፍ ስለ ጉቦ አቀባባዩችና ድርጊቱን መፈፀም ስለሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት አናነሳለን። ስለ ጉቦ ካነሳን አይቀር በቅድሚያ እዚሁ ማህበራዊ ሚድያው ላይ ያገኘናትን  ጉቦ በፍትሕ ሂደት ውስጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅእኖ የምትገልፅ ጨዋታ እናካፍላችሁ ፡፡

የጉቦ በር

ሰውየው ሀቀኛ የወልድያ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ቤታቸው የሚገኘውም ከወልዲያ ከተማ ወጣ ብሎ ገብርኤል ተብሎ በሚጠራው መንደር ነው ፡፡ ከጎረቤታቸው ጋር በድንበር ግጭት ተካሰሱና ወልዲያ ከተማ በሚገኘው ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ቀጣዩን ቀጠሮ ሲጠባበቁ ከውስጥ አዋቂ ‘‘ዳኛው ካባለጋራቸው ጉቦ መቀበሉንና በክርክሩ እንደሚሸነፉ’’ ወሬ ሰሙ። ይሄኔ ወደ ፍርድ ቤቱ የሚወስዱት ሁለት ብቸኛ የመንገድ አማራጮች ትዝ አሉዋቸው፡፡ አንዱ በ ’ንፍጥ ድንጋይ ወንዝ በኩል ሲሆን ሌላኛው በጥቁር ውሀ ወንዝ በኩል ‘ጉቦ በር’ ተብሎ በሚጠራው መንገድ ነው፡፡ የቀጠሮው ቀን ባለጋራቸው ቀድሟቸው ደርሶ ውሳኔው ከተነበበለት በኋላ ዘግይተው ደረሱ። ዳኛው ‘‘ምነው ዘገዩ?’’ ሲላቸው ፡፡

‘‘አይ እኔ በዋናው መንገድ በኩል ስመጣ ባለጋራዬ ባቋራጭ ‘በጉቦ በር’ መጥቶ ነው የቀደመኝ’’ ብለው በአሽሙር ዳኛው ጉቦ መብላቱን ማወቃቸውን ነገሩት፡፡

የጉቦ በር ፍትሕን ማዛቢያ አቋራጭ ነው፡፡ በእውነት፣ በሀቅ፣ በማስረጃ ፣በቀጥተኛው መንገድ መብትን ከማስጠበቅ ወይም ግዴታን ከመወጣት በተወገዘውና በተከለከለው ድብቅ አቋራጭ መሹለክ ነው፡፡ የጉቦ በሮች አንዳንዴ ሚከፈቱት በአቀባባዮች ነው ፡፡ ስለ አንድ ጉቦ አቀባባይ እውነተኛ የፍርድ ሂደትና በመጨረሻው የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ጉቦ ማቀባበልን ብቻ የተመለከተ የተሰጠ አስገዳጅ ውሳኔን ደግሞ ቀጥሎ እንመለከታለን።

ጉቦ አቀባዩ ጠበቃ

አቶ አትክልት በጉምሩክ በወንጀል ተጠርጥረው ይፈለጉ ነበር፡፡ ስማቸው ይቅርብንና አንድ ታዋቂ ጠበቃ ሊረዷቸው ፈለጉ። እርዳታቸው ግን በፍትሕ አደባባይ ሕጉን ጠቅሶ ማስረጃ አቅርቦ የሚደረግ የሀቀኛ ጠበቃ እርዳታ ሳይሆን ‘በጉቦ በር’ በኩል ባቋራጭ ሾልኮ ፍትሕን ለማዛባት የተደረገ ሙከራ ነበር ፡፡

የአቶ አትክልትን ጉዳይ የያዘውን የጉምሩክ አቃቢ ሕግ አቶ ተስፋማሪያም ገ/ትንሳኤን ህሊናውን ሸጦ ሙያውን አቃሎ መዝገቡን ሕጉ በማይፈቅደው መልኩ እንዲዘጋውና ለወረታው አምስት ሺህ ብር እንዲቀበላቸው በተደጋጋሚ ወተወቱት ፡፡ ለሙያው ታማኝና ሀቀኛው ዐቃቢ ሕግ ተስፋማሪያምም ቀጠሮ ሰጣቸው።

መስከረም 24 2003 ዓ.ም ሀያሁለት ጌታሁን በሻህ ህንፃ 3ኛ ፎቅ ላይ የሚገኝ ካፌ ውስጥ ከቀኑ 10፡30 ሀቀኛው ዐቃቢ ሕግና  ጉቦ አቀባዩ ጠበቃ ተገናኙ። ጉቦ አቀባዩ ጠበቃም 5ሺህ ብሩን አውጥተው ሲሰጡት ዐቃቢ ሕጉ ቀድሞ ባሳወቃቸው ሲቪል ለባሽ ፖሊሶች እጅ ከፍንጅ ተይዘው በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

ጉቦ አቀባዩ ጠበቃ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጉቦ በማቀባባል ወንጀል ተከሰሱ። ክሱን ክደው ቢከራከሩም ፍርድ ቤቱ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ጉቦ ማቀባበላቸውን በማስረጃ ስላረጋገጠ የአንድ አመት ከሁለት ወር ፅኑ እስርና የሦስት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ወሰነባቸው፡፡

ጉቦ አቀባባዩ ጠበቃ በሁለት ጠበቆች ተወክለው እስከ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቢከራከሩም ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰ/መ/ቁ 78793 ሰኔ 21 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት የተጣለባቸውን ቅጣት አፀናውና ወህኒ ወረዱ ፡፡ (ውሳኔው ቅፅ 13 የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች ላይ ታትሞ ወጥቷል።)

ጉቦ ማቀባበል በወንጀል ሕጉ

ጉቦ አቀባዩ ጠበቃ የተቀጡበት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 429 ‘‘ማንኛውም ሰው ለራሱ ጥቅም ቢያገኝም ባያገኝም፣ የመንግስት ሥራን ለሚያከናውን ሰው ጉቦ ለመስጠት ገንዘብ፣ ዋጋ ያለው ነገር፣ አገልግሎት ወይም ሌላ አይነት ጥቅም ከሌላ ሰው የተቀበለ ከሆነ ወይም የራሱን የባንክ ሂሳብ ለእንደዚህ አይነት ጉቦ ለማቀባበል ካዋለው ይቀጣል’’ ይላል፡፡

ጉቦ ተቀባዮችም ሆነ ሰጪዎች ከህዝብ ዓይን ለመሸሽና ተጠያቂነትን ለማምለጥ በተለይ ከተቀባዩ ጋር ቅርበት ወይም የሥራ ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች ይጠቀማሉ፡፡ ሁሉንም ማለት ባይቻልም በጉዳይ አስፈፃሚነት እና በጉዳይ ገዳይነት (ጉገ) ስም ጉቦ ማቀባበሉን የሚያሳልጡ እንዳሉ ይታወቃል ፡፡

‹‹ጉዳይህ ያለበት ተቋም ውስጥ ወሳኝ ሰው ስላለኝ በኔ ጣለው!›› ብለው በልበ ሙሉነት የሚናገሩ ሰዎችንም “ብቻ እናንተ ይሄን ያል ብር አዘጋጁ’’ ካሏችሁ ጠርጥሩ ጉቦ ሊቀበሏችሁ ወይም ሊያቀባብሉ  ይሆናል፡፡

‘‘እከሌ የተባለውን የመንግስት ሠራተኛ ታውቀዋለህ/ሽ አይደል? አንተ/ቺ ስለምትቀርበው/ቢው እስቲ ይቺን ስጥልኝ/ጪልኝ፡፡’’ የሚል ካጋጠማችሁም ጠርጥሩ። ሳታስቡት ጉቦ አቀባባይ ሊያረጓችሁ ይችላሉ፡፡ ሲጀመር ‘ለምን ይሰጠዋል?’ ሲቀጥል ‘መስጠት አለብኝ ካሉም ልስጥ ባዮቹ ለምን እራሳቸው አይሰጡም?’’ ብላችሁ ጠይቁ።

ለማንኛውም ጉቦ ማቀባበል በወንጀል ሕጉ እንደ ነገሩ ክብደት ማለትም (እንደ ጉዳዩ፣ የገንዘቡ መጠን እና እንደሚያደርሰው ጉዳት) እየታየ ከቀላል እስር አንስቶ እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስር እና በገንዘብ ቅጣት ያስቀጣል።

የዐቃቢ ሕጉ የተስፋ ማርያም ገብረትንሳኤ አይነቶቹ ጉቦን የሚዋጉና የሚያጋልጡ ሀቀኛ ዜጎችና የሀገር ባለውለታ ጀግኖች ናቸው።ሊመሰገኑና ሊከበሩ ይገባል።

ከጉቦ ጋር በተያያዘ የታዘባችሁት የአሰራር ክፍተት፣ያጋጠማችሁ ገጠመኝ ካለ አጋሩንና እንወያይበት።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top