የከተሞች ወግ፡- ሌጎስ

6 Mons Ago
የከተሞች ወግ፡- ሌጎስ

የአፍሪካ የጥበብ ማዕከል፤ በምእራብ አፍሪካ ረዥሙ ህንፃ መገኛ፤ የባህል፣ የሃይማኖት እና የቋንቋ ብዝኀነት ተከባብረው በሰላም የሚኖሩባት፤ የቀጠናው የኢኮኖሚ ማዕከል ናት - ሌጎስ።

በፖርቹጋል ቋንቋ ሌጎስ ማለት ሀይቆች ማለት ሲሆን፤ በናይጄሪያ ከሚገኙ 36 ክልሎች መካከል አንዷ የሆነችው የሌጎስ ግዛት ዋና ከተማ ናት።

መገኛዋ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጄሪያ፤ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ ሲሆን፤ ከ20 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይኖርባታል። ስፋቷ 1 ሺህ 171 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው።

ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ ኖሊውድ በሚል ለሚታወቀው የናይጄሪያ የፊልም ኢንዱስትሪ ዕድገት አስተዋፅኦ በማድረግ ተጠቃሽ ናት - ሌጎስ።

የተመሰረተችው በ15ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን፤ ናይጄሪያ ዋና ከተማዋን ወደ አቡጃ ከማዛወሯ በፊት ከ1861-1991 የሀገሪቱ ዋና ከተማ ሆና አገልግላለች።

በሀገሪቱ አንጋፋ የሆነው የሌጎስ ዩኒቨርሲቲ፣ የሌጎስ ብሔራዊ ሙዚየም፣ ሙርታላ ሙሐመድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ናይጄሪያ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ መውጣቷን ለመዘከር የተሰየመው የነፃነት አደባባይ በከተማዋ ይገኛሉ።

የባህል፣ የሃይማኖት እና የቋንቋ ብዝኀነትን በሰላማዊ መንገድ በማስተናገድ ትታወቃለች።

በትወና፣ በሙዚቃ፣ በኮንሰርት፣ በኮሜዲ እና በሌሎችም የጥበብ ስራዎች አንጋፋ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሀገሪቱ የጥበብ ዕድገት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ የሚገኘው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቴአትር መገኛም ነች - ሌጎስ። 

ናይጄሪያን የፈጠራና የጥበብ እምብርት ለማድረግ በአዲስ መልክ እያታደሰ የሚገኘው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቴአትር፤ ናይጄሪያን የአፍሪካ የመዝናኛ ማዕከል እንድትባል አስችሏታል። 

ከተማዋ በርካታ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች እና ብዙ ቢሊየነሮች የሚገኙባት ከተማ ናት።

ከተማዋ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች፣ የጎልፍ ክበባት እና ጥራት ያላቸው ምግብ ቤቶች መገኛ በመሆኗ ለመዝናኛ ተመራጭ ናት። በከተማዋ ወደቦች በሚዘጋጁት መዝናኛ የጥበብ ድግሶች ሰዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በደስታ ያሳልፋሉ።

የሌጎስ ወደብ በአፍሪካ ከሚገኙ አስር ግዙፍ ወደቦች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ለሀገሪቱ የውጭ ንግድ ቁልፍ ሚና አለው። ናይጄሪያ ከውጭ ከምታስገባው ምርት 80 በመቶ እንዲሁም ወደ ውጪ ከምትልከው ሸቀጥ 70 በመቶ የሚሆነው የሚያልፈው በሌጎስ ወደብ  ነው።  

የሌጎስ ጎዳናዎች የመንገድ ዳር ፈጣን ምግቦች የሚዘወተሩባቸው እና ማንኛውም እግር የጣለው ተላላፊ መንገደኛ የሚፈልጋቸውን ጣፋጭ ምግቦች የሚያጣጥምባቸው ናቸው። ከተማዋ የትራፊክ እንቅስቃሴ የምትቆጣጠርበት ዘመናዊ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ስርዓትም  ዘርግታለች። 

ነዳጅ፣ ጋዝ፣ የትራንስፖርት እና የፋይናንስ አገልግሎትች ማዕከል፤ የበርካታ ድርጅቶች መገኛ፣ የቀጠናው የኢኮኖሚ ሞተርም ናት።

ሰዎች የሚኖሩባት ተንሳፋፊ ትንሽ ከተማ፣ በርካታ ሚሊየነሮችን የያዘች ባላት የመዝናኛ እና የስራ እንቅስቃሴ በአፍሪካ የማታንቀላፋዋ ከተማ በሚልም ትታወቃለች - ሌጎስ።

በላሉ ኢታላ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top