ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ አገራት የነበራቸው ጉብኝትና የጉባዔ ተሳትፎ የኢትዮጵያን ክብርና መልካም ገጽታ ከፍ ያደረገ ነው - ዶክተር ለገሰ ቱሉ

7 Mons Ago
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ አገራት የነበራቸው ጉብኝትና የጉባዔ ተሳትፎ የኢትዮጵያን ክብርና መልካም ገጽታ ከፍ ያደረገ ነው - ዶክተር ለገሰ ቱሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሣምንት በኦስትሪያ እና በቼክ ሪፐብሊክ ያደረጉትን ቆይታ እና በኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ የነበራቸውን ተሳትፎ በማስመልከት የመንግሥት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው በኦስትሪያ ቪዬና የመንግስታቱ ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጉባዔ፣ በዱባይ 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ የመሪዎች ጉባዔ ተሳትፎ እንዲሁም በቼክ ሪፐብሊክ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

አካታችና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል በመከረው በቪዬናው የኢንዱስትሪ ልማት ጉባዔ፥ ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት የዘርፉ ስኬታማ ልምዶች የቀረቡበት መሆኑን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያም ባለፉት አምስት ዓመታት መዋቅራዊ እና የሴክተር ማሻሻዎችን ጨምሮ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እንዲሁም በተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ በርካታ ተሞክሮዎቿን አቅርባ አድናቆት የተቸረችበት እንደሆነም አንስተዋል።

የ140 ሀገራት መሪዎችና ከ90 ሺህ በላይ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት እና በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ዱባይ በተካሄደው 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ የመሪዎች ጉባዔ ላይም የኢትዮጵያ ተሞክሮ መቅረቡን ገልጸዋል።

የሀገራት መሪዎች ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር ከተናጠላዊ ይልቅ የተቀናጀ የመፍትሄ እርምጃ ውጤታማ እንደሚያደርግ መግለፃቸውን አስታውሰዋል።

በአየር ንብረት ቀውስ ታዳጊ ሀገራት ለሚደርስባቸው ጉዳት የበለጸጉ ሀገራት እንደ ችሮታ ሳይሆን እንደ ግዴታ ወስደው መደገፍ እንደሚገባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመድረኩ አንስተዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ እና በሌማት ትሩፋት እንዲሁም በስንዴ እና በአትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነት የተገኙ አመርቂ ውጤቶች በአብነት በመጥቀስ ኢትዮጵያ በዘርፉ ተግባራዊ እርምጃን አስቀድማ እየወሰደች መሆኑን ማውሳታቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን መሰል ስኬታማ ስራ የሰሩ ሀገራት ሊደገፉ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ዶክተር ለገሰ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ ተሞክሮ በዱባይ በመካነ ርዕይ ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጎ የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች መጎብኘቱን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትና የጉባዔ ተሳትፎ የኢትዮጵያን ክብርና መልካም ገጽታ ከፍ ያደረገ እንደነበር አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቼክ ሪፐብሊክ በነበራቸው የስራ ጉብኝት የኢትዮ-ቼክን ታሪካዊና ነባር የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ከሀገሪቱ መሪ ጋር መምከራቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም፥ ከቼክ ሪፐብሊክ ባለሀብቶች ጋር ውይይቶች ስለማድረጋቸው አስታውሰው፤ በተለያዩ ታሪካዊ እና አምራች ኢንዱስትሪዎች ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ሁለቱ ሀገራት በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸው፤ ጉብኝቱም የተሳካ ነበር ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top