ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም” ግንባታ የሚገኝበትን ደረጃ በዛሬው እለት ጎብኝተዋል።
አንቲባዋ ጉብኝታቸውን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልእክት "ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን ታሪክም እየገነባን ነው!" ብለዋል።
የአድዋ ድልን ታሪካዊ ዳራ መነሻ አድርጐ እየተገነባ የሚገኘው አድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም የኢትዮጵያ ጀግኖችንና የአድዋ መልክዓ ምድርን በሚገልፅ መልኩ ታሪካዊ እሴቱን ጠብቆ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ነው ያሉት አንቲባ አዳነች።
ሙዚየሙ በከተማችን ውስጥ እስከዛሬ ከተገነቡ እና በመገንባት ላይ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ግዙፉ ሲሆን 11 ብሎኮችን የያዘ 45 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እየተገነባ ያለ ሙዚዬም ነው።
ሙዚዬሙ በውስጡ የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮችን፣ የአድዋ ፈረሰኞች ማስታወሻ፣ ለሴት ጀግኖች ክብር የተሰየመ ማስታወሻ፣ የአንድነት ማዕከል፣ የአፍሪካ ነፃነት ማስታወሻ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጀግኖችን ጉዞ የሚያሳይ ሙዚየም እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ከ300 እስከ 4000 ሰው ድረስ የሚይዙ የተለያዩ አዳራሾች ይገኝበታል ተብሏል።
ግንባታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት የሚደረግ ይሆናል ያሉት ከንቲባዋ መጪውን የአድዋ በዓል የጥቁር ህዝቦች የድል የታሪክ ከፍታን በሚመጥን መልኩ በዚሁ ስፍራ ላይ በጋራ እናከብራለን ብለዋል።