የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የፍላጎት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው: - አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

11 Mons Ago 1060
የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የፍላጎት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው: - አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የፍላጎት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለፁ።

አዲስ አበባ ተቀማጭነታቸውን ላደረጉ የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችውን የባሕር በር ስምምነት በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ከአላማው ውጪ የሆኑ የተሳሳቱ መረጃዎች መሰራጨታቸውን አንስተው የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የፍላጎት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በጅቡቲ ወደብ በኩል የገቢ ወጪ ንግዷን እያከናወነች መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ካለው አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ አማራጮችን መፈለግ ግድ ይላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም እና ፀጥታ የሕይወት መስዕዋትነት መክፈሏን ጠቅሰው ከሶማሊያም ሆነ ከሌሎች ጎረቤት አገራት በጋር ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

ከሶማሊ ላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር እና ኢኮኖሚ ምላሽ መስጠትን ዓላማ ያደረገ እንጂ ማንንም ለመጉዳት አይደለም ሲሉም አስረድተዋል።

የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተመለከተም ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለክልሉ አመታዊ በጀት ከመመደብ ጀምሮ በጦርነቱ ሙሉ ለሙሉና በከፊል የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም መንገድና ድልድዮችን ጨምሮ ባንክ ቴሌኮምና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች መጀመራቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ ተከስቶ በነበረው ጦርነት ወንጀል የፈፀሙ አካላት ላይ አስፈላጊው ማስረጃ በማጠናከር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ክልሉንና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ አለም አቀፍ አጋር አካላት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም አንስተዋል።

የሰላም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም አምባሳደር ሬድዋን አብራርተዋል

በአማራ ክልል የነበረው የጸጥታ ችግርም በመከላከያና በክልሉ የፀጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋሉን አብራርተዋል።

መንግስት ማንኛውንም ችግር በውይይትና በድርድር እንጂ በአፈ-ሙዝ የመፍታት አላማ የሌለው መሆኑን ገልጸው በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማድረጉን ተናግረዋል።

በአሁን ጊዜም በክልሉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን አብራርተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልልም ተመሳሳይ የጸጥታ ስራዎቸን ለማከናወን የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

 እንዲ ዓይነት አደረጃጀቶች ህዝቡን ከማሸበርና የራሳቸውን ጥቅም ከማስጠበቅ ውጪ ዓላማ የሌለው ነው ብለዋል።

የትጥቅ እንቅስቃሴን አማራጭ የሚያደርግ አካልም በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በኩል ለመነጋገርና መዘጋጀት አለበት ነው ያሉት።

የመከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ፤ በሰሜኑ ወታደራዊ አታሼዎችና አለም አቀፍ ተቋማት ለኢትዮጵያ ሰላምና ልማት እያበረከተ ላለው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

ወታደራዊ አታሼዎች የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔት በተመለከተ በየማህበራዊ ሚዲያ የሚነዙ የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን ለማጥራት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ከመከላከያ ወታደራዊ አመራሮች እውነተኛ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚችሉም ነው የገለጹት።

የየአገራቱ ወታደራዊ አታሼዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ ላይ ያለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶ በተደረገው ገለጻ ትክክለኛ መረጃ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

መንግስትና የመከላከያ ሰራዊቱ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ  ያሳዩት ቁርጠኝነትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top